ከብ/ጄኔራል ከማል ገልቹና ብ/ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ሹመት ጀርባ?

የፎቶው ባለመብት, OBS/BBC
ከዓመታት በፊት መቶ ሃምሳ የሚሆኑ ወታደሮችን ይዘው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር(ኦነግን) የተቀላቀሉት፣ ከዚያም ከኦነግ ወጥተው የራሳቸውን ፓርቲ ያቋቋሙትና በቅርቡ ወደ አገራቸው የተመለሱት ብርጋዴር ጀነራል ከማል ገልቹ የኦሮሚያ ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ሆነው የመሾማቸው ነገር የተሰማው ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ነበር።
በሌላ በኩል በመፈንቅለ መንግሥት ተከስሰው ዘጠኝ ዓመታትን በእስር ያሳለፉትና በቅርቡ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ማእከላዊ ኮሚቴ አባል ሆነው የተመረጡት ብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው ፅጌ የአማራ ክልል ፅጥታ ቢሮ ኃላፊ ሆነው መሾማቸው የተሰማው በተመሳሳይ ጊዜ ነበር።
የሹመቱን ዜና ተከትሎ ብዙ መላምቶች መሰንዘራቸው አልቀረም።
የጄኔራል ከማል ገልቹን ሹመት እሾህን በሾህ ነው የሚሉ አንዳንዶች ከኦነግ አብራክ የወጡት ከማል ገልቹን እዚህ ኃላፊነት ላይ ማስቀመጥ ትጥቅ ለመፍታት አንገራግሯል የተባለውን ኦነግን ቀስ በቀስ ለመግራት ሁነኛ ዘዴ ነው ያሉም አሉ።
በእንግሊዙ ኪል ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት እንደ ዶ/ር አወል ቃሲል አሎ ያሉ ፖለቲካ ተንታኞች ደግሞ በዚህ ሐሳብ አይስማሙም።እንዲያውም ሹመቱ ከኦነግ ትጥቅ መፍታትና አለመፍታት ጋር የሚያያዘው ምንም ነገር የለም ይላሉ።
"...ስለ ኦነግ ሌላ ሰው የሌለው እሳቸው ብቻ ያላቸው ዕውቀት ይኖራል ብዬ አላስብም"በማለት ሹመቱን ለኦነግ የተሰጠ አጸፋ አድርገው እንደማያዩት ያስቀምጣሉ።
ሹመቱ አስገርሟቸው ከሆነ የተጠየቁት ዶ/ር አወል "ከዚህ ሥርዓት ጋር ትልቅ ተቃርኖ የነበረው፣ የራሱን ፓርቲ አቋቁሞ በውጭ አገር ይንቀሳቀስ የነበረና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም እንደ ጠላት ይታይ የነበረ ግለሰብ ወደ አገር ቤት ተመልሶ በአጭር ጊዜ ውስጥ የአንድ ክልል መንግሥት የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ መሆን" በተወሰነ መልኩ ሊያስገርም እንደሚችል ይገልፃሉ።
በአንጻሩ ደግሞ የአገሪቱ የፖለቲካ ሁለንተና እየተቀየረ ያለበት ፍጥነት ሲታይ ነገሩ ብዙም የሚገርም እንዳልሆነ ያወሳሉ።
የብ/ጄኔራል ከማል ገልቹ ሹመት ምን ዓይነት ትርጉም ነው የሚሰጥዎት? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ዶ/ር አወል "ከኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(ኦዴፓ) እምብዛምም የተለየ ፕሮግራም ከሌላቸው ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር አንድ ሆኖ የመሥራት ነገር በብዙ ሰዎች ሲነገር ነበር።" ካሉ በኋላ በፓርቲዎቹም መካከል ንግግር ተጀምሮ እንደነበር በግል እንደሚያውቁ ጠቅሰዋል።
ስለዚህም ሹመቱ ለሳቸው የሁለቱ ፓርቲዎች ንግግርና አብሮነት የወለደው እና የጄኔራሉ ልምድና ብቃት ላይ የተመሠረተ ነው።
በሌላ በኩል ምንም እንኳ የፕሮግራም ልዩነት ባይኖራቸውም ኦሮሚያ ላይ የተለያዩ ፓርቲዎች በተናጥል መንቀሳቀሳቸውን ተከትሎ በፓርቲዎቹ ላይ ሥርዓቱ የኔ ነው የሚል የባለቤትነት መንፈስ ለመፍጠርና ወደ አንድ ለማምጣት ታስቦበት የተደረግ ሊሆን እንደሚችልም ይገምታሉ።
ኦሮሚያ ላይ የሚንቀሳቀሱና ሰፊ ደጋፍ ያላቸው እንደ ኦነግ እና ኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ለሹመት ባልተጋበዙበት ሁኔታ የብ/ጄኔራል ከማል ገልቹ ሹመት ምን ያሳያል?
ዶ/ር አወል እንደሚያምኑት ነገሩ የሚያሳየው ከኦዴፓ ጋር ንግግር ላይ ከነበሩትና ለመቀላቀል ከተስማሙት መካከል የብ/ጄኔራል ከማል ገልቹ ፓርቲ መግባባት ላይ መድረሱ ነው። ሹመቱም በዚሁ አንፃር የሄደ ነው።
በጆርጂያ ጉኔት ኮሌጅ የፖለቲካ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ዮሐንስ ገዳሙም የጄኔራል ከማል ገልቹ ሹመት አጠቃላይ በአገሪቱ ያለው የለውጥ መንፈስ የወለደው ነው ብለው ያምናሉ።
የ"ባላንጣዎች ጥምረት" በምዕራቡ ዓለምም ያለ አሠራር እንደሆነ የጠቀሱት ዶ/ር ዮሐንስ ሹመቱ "በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ያለውን ማኅበረሰብ ፍላጎት ለማሟላት በጋራ የምንሠራና ጥያቄዎቻችሁን ለመመለስ የምንሞክር ነን" የሚል መልእክት ያለው ነውይላሉ።
በተለይም ኦሮሚያ ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኃይል ክፍፍል አለ እየተባለ የሚነገረውን ነገር ለማስተካከል የተወሰደ እርምጃ ሊሆን እንደሚችልም ይገምታሉ፤ ዶ/ር ዮሐንስ።
የብ/ጄኔራል ከማል ገልቹም ሆነ የብ/ጀነራል አሳምነው ፅጌ የፀጥታ ተቋማትን እንዲመሩ መሾም የፀጥታ ተቋማትን ከፓርቲ ፖለቲካ ነፃ የማድረግ የመንግሥት ፍላጎትን ጥያቄ ውስጥ አይከተውም ወይ የሚል ጥያቄ የተነሳላቸው ዶ/ር ዮሐንስ "የኢትዮጵያ የፀጥታም ሆነ ማንኛውም አስተዳደራዊ ጉዳይ ከፖለቲካ ፓርቲ ተፅእኖ በፍፁም ሊወጣ አይችልም" በማለት ይመልሳሉ። ይህ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው የርዕዮተ ዓለም ለውጥን ተከትሎ ነው ባይ ናቸው።
"ዛሬም ሥልጣን ላይ ያለው ኢህአዴግ ነው።ምንም እንኳ አሳማኝ የሚባሉ ለውጦችን እያደረገ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ባህሪውን ይቀይራል ብዬ አላምንም"
በከፍተኛ አመራር ደረጃ የፓርቲና የመንግሥት አስተዳደር መስምርን እንለያያለን ብለው ቃል ቢገቡም መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን ይህን እንዲያደርጉ የሚፈቅድ አይደለም የሚሉት ዶ/ር ዮሐንስ ዞሮ ዞሮ ተሿሚዎቹ የፓርቲያቸውን ፍላጎት እንደሚያስፈፅሙና ከፓርቲያቸው ተጽእኖ ሊላቀቁ የሚችሉበት ዕድል እንደሌለ ይደመድማሉ።












