ፈረንሳይ እስላማዊ ጽንፈኝነትን ለመግታት አዲስ ሕግ አረቀቀች

የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን

የፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን ካቢኔ በፈረንሳይ ጽንፈኛ እስላማዊነትን ይገታል ያሉትን አዲስ ሕግ አረቀቁ።

በቅርቡ ፈረንሳይ በጽንፈኞች ተደጋጋሚ ጥቃትን ስታስተናግድ ቆይታለች።

ረቂቅ ሕጉ ሰዎች በሃይማኖት ጉዳይ የተሰማቸውን እንዲገልጹ የሚፈቅድ ከመሆኑም በላይ ታዳጊዎችን በቤት ማስተማር ላይ ጥብቅ ክልከላዎችን ይጥላል ተብሏል።

የፈረንሳይ መንግሥት ሃይማኖትን ለማጥቃት ያወጣው ሕግ ነው በማለት በርካቶች ረቂቅ ሕጉን ተችተዋል።

የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚንሰትር ጄን ካስቴክ ግን ሕጉ ሙስሊሞችን ከጽንፈኞች ነጻ የሚያደርግ ሕግ ነው ብለዋል።

"የሪፐብሊካን መርሆችን" ይደግፋል የተባለው ረቂቅ ሕግ፤ በኢንተርኔት የሚፈጸሙ የጥላቻ ንግግሮች በጥብቅ እንዲመረመሩ ያዛል እንዲሁም በኢንተርኔት አማካይነት የሰዎችን ግላዊ መረጃ ማጋለጥን ይከለክላል።

ከሳምንታት በፊት የነብዩ መሐመድን የካርቱን ምስል ለተማሪዎቹ ማሳየቱን ተከትሎ የተገደለው ሳሙኤል ፓቲ፤ በኢንተርኔት አማካኝነት ዘመቻ ተፍቶበት ነበር ተብሏል።

ረቂቅ ሕጉ በኢንተርኔት አማካይነት የሰዎችን ግላዊ መረጃ ማጋለጥ የከለከለው ለዚሁ ምላሽ እንዲሆን ነው ተብሏል።

ሕጉ "ሚስጥራዊ" በሆነ መልኩ እስላማዊ አስተምሮ የሚሰጡ ትምህርት ቤቶችን ያግዳል።

ይህም ብቻ አይደለም ከአንድ ሰው በላይ ጋር ትዳር መመስረት ሕጉ አይፈቅድም። ከአንድ ሰው በላይ የትዳር አጋር ላላቸው አመልካቾች ፈረንሳይ የመኖሪያ ፍቃድ እንደማትሰጥ በረቂቅ ሕጉ ተጠቅሷል።

በሴቶች ላይ የድንግልና ምርመራ የሚያደርጉ የጤና ባለሙያዎች ቅጣት ይጣልባቸዋል። ከፍ ሲልም የሥራ ፍቃዳቸውን ሊነጠቁ ይችላሉ ተብሏል።

ሙስሊም ማህበራት የፋይናንስ ምንጫቸው እና ወጪያቸው ግልጽነት የተሞላበት እንዲሆን ግዴታ ጥሏል ሕጉ።

ፈረንሳይ ይህን መሰል ሕግ ለማውጣት ስታጤነው የቆየችው ጉዳይ ቢሆንም በቅርቡ በፈረንሳይ የደረሱ ጥቃቶች ሕጉ በፍጥነት እንዲወጣ አስገድደዋል።

በቅርቡ በፓሪስ እና በመዲናዋ አቅራቢያ በጽንፈኛ ሙስሊሞች የተፈጸሙት ጥቃቶች የአገሪቱን ዜጎች አስቆጥተዋል።

ፈረንሳይ ወደ 5 ሚሊዮን የሚጠጉ ሙስሊሞች የሚኖሩባት አገር ናት።