የባይደን ልጅ ላይ የግብር ምርመራ እየተካሄደ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ሆነው የተመረጡት የጆ ባይደን ልጅ፤ ሀንተር ባይደን የግብር ምርመራ እየተካሄደበት መሆኑን አስታወቀ።
ምርመራው እየተከናወነ የሚገኘው ዳልዌር ባሉ ዐቃቤ ሕጎች ነው።
ሀንተር ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት እንደሰጠና ምርመራው ገለልተኛ ከሆነ ምንም ሕገ-ወጥ ተግባር እንዳልፈጸመ እንደሚታወቅ ገልጿል።
ጆ ባይደን "ልጄ ብዙ ነገር አሳልፏል። ባለፉት ጥቂት ወራት ጥቃት ሲሰነዘርበት ነበር። ግን አልሰበረውም። እኮራበታለሁ" ሲሉ ሀንተርን አሞግሰዋል።
ሀንተር ስለ ምርመራው ዝርዝር መረጃ አልሰጠም።
የ50 ዓመቱ የባይደን ልጅ በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት በተደጋጋሚ የሪፐብሊካኖች ትችት ኢላማ ሆኗል።
በተለይም ሃንተር በዩክሬን እና ቻይና ባለው የንግድ ተሳትፎ ሲብጠለጠል ቆይቷል። በባራክ ኦበማ ዘመነ መንግሥት ምክትል ፕሬዘዳንት የሆኑት ባይደን ስማቸው ከቢዝነሶቹ ጀርባ ይነሳል።
ዶናልድ ትራምፕ ዩክሬን የባይደን ቤተሰብ ላይ ምርመራ እንድታደርግ ጫና ፈጥረዋል በሚል ባለፈው ዓመት ምርመራ ተደርጎባቸው እንደነበር ይታወሳል።
ሆኖም ግን ትራምፕ ነፃ ተብለው ምርመራው ተገባዷል።
ባይደን ካቢኔያቸውን እያዋቀሩ ሳለ ነው ልጃቸው ላይ ምርመራ መከፈቱ የተሰማው።
በቀጣዩ ወር ባይደን በዓለ ሲመታቸው ሲከናወን ምርመራው ካልተጠናቀቀ፤ ምርመራውን የሚመሩት ባይደን የሚመርጧቸው ዐቃቤ ሕግ ይሆናሉ።
ሀንተር ላይ ምርመራ ሊደረግ እንደሚችል የሚጠቁሙ መረጃዎች ለወራት ሲወጡ ነበር።
ምርመራው እንዲካሄድ ትራምፕ ጫና አሳድረዋል ሲሉ የሚወቅሷቸው ቢኖሩም፤ ምርመራውን የሚመሩት ዐቃቤ ሕግ ዴቪድ ዌይስ በሙያው የተከበሩ ናቸው።
ዐቃቤ ሕጉን የመረጧቸው ትራምፕ ቢሆኑም፤ በኦባማ አስተዳደር ምክትል ዐቃቤ ሕግ ሆነው አገልግለዋል።












