ቱርክ ፕሬዚዳንቷን አዋርዷል ያለችውን የፈረንሳይ መፅሄት ልትከስ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የፈረንሳዩ መፅሄት ቻርሊ ሄብዶ የቱርክን ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋንን ክብር በሚነካ መልኩ የካርቱን ምስል አትሟል በሚል ቱርክ ህጋዊ እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ እርምጃዎችን እንደምትወስድ ቃል ገብታለች።
በካርቱኑ ምስል ላይ የቱርኩ ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን የጠመጠመችን ሴት ቀሚስ ሲገልቡ ያሳያል።
የቱርክ ሚዲያዎች እንደዘገቡት ከሆነ የአገሪቱ አቃቤያነ ህግ በቧልተኛው መፅሄት ላይ ይፋዊ የሆነ የምርመራ ፋይል መክፈታቸውን ነው።
በቱርክ መንግሥት ባለስልጣናት መካከል ከፍተኛ ቁጣም ቀስቅሷል።
የፕሬዚዳንቱ ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ፋህረቲን አልቱን"ቻርሊ ሄብዶ ፕሬዚንዳንቱ ላይ ያነጣጠረ አፀያፊ የካርቱን ምስሎችን አትሟል። መፅሄቱ እነዚህን አፀያፊ ምስሎች በማተም የሚያደርገውን የባህል ዘረኝነትና ጥላቻ ማስፋፋት እናወግዛለን" ብለዋል።
የአገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንትም እንዲሁ ይህንን ክብር የሚያዋርድ ምስልን በመቃወም ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ጥሪ አቅርበዋል።
"የማሰብና የመናገር ነፃነት በሚል ሽፋን ስም በመደበቅ የሚሰራው ስራ ማንንም አያታልልም" ብለዋል ምክትል ፕሬዚዳንቱ በትዊተር ገፃቸው
የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን "ፅንፈኛ ሙስሊሞች" ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ እወስዳለሁ ማለታቸውን ተከትሎ በፈረንሳይና በቱርክ መካከል ውጥረት ነግሷል።
በኔዘርላንድ ባለ ፀረ እስላም የፓርላማ አባልም ከካርቱን ጋር በተገናኘ ክስ የመመስረት ሂደት ላይ ያሉት ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን የፈረንሳይ ምርቶች ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን ፕሬዚዳንት ማክሮንንም "የአእምሮ ምርመራ ያስፈልጋቸዋል" ብለዋል።
ውጥረቱ በቱርክና በፈረንሳይ መካከል ብቻ ሳይሆን በርካታ የእስልምና እምነት ተከታዮች ባሉዋቸው ባንግላዴሽ፣ ኩዌት፣ ዮርዳኖስና ሊቢያ በመሳሰሉት አገራትም የፈረንሳይ ምርቶችን አንገዛም በሚል የማእቀብ ጥሪ ተደርጓል።
ውዝግቡ በተለይ የተጧጧፈው የነብዩ መሃመድን ካርቱን በክፍል ውስጥ በማሳየቱ በአሰቃቂ ሁኔታ ተቀልቶ የተገደለው ፈረንሳያዊው መምህርን ተከትሎ ፕሬዚዳንቱ ባደረጓቸው ንግግር ነው።
ፕሬዚዳንት ማክሮን መምህር ሳሙኤል ፓቲ "የተገደለበት ምክንያት የእስልምና እምነት ተከታዮች የወደፊቱ እጣ ፈንታችንን መቆጣጠር ስለሚፈልጉ ነው። ፈረንሳይ ካርቱኗንም ቢሆን አሳልፋ አትሰጥም" ብለዋል።
የነብዩ መሃመድን ምስል በየትኛውም ሁኔታ ማሳየት በእስልምና እምነት ነውርና አፀያፊ ተደርጎም ይቆጠራል። ሆኖም ፈረንሳይ ከእምነት ውጭ ያለ አገዛዝን እንደመከተሏ መጠን የመናገር ነፃነትን የሚቀለብስ ነው ነው በማለትም ትከራከራለች።












