ትግራይ ፡ በተባበሩት መንግሥታት ሰራተኞች ላይ እንደተተኮሰባቸው ኢትዮጵያ አረጋገጠች

የኢትዮጵያ ወታደር

የፎቶው ባለመብት, AFP

ትግራይ ውስጥ የኢትዮጵያ ወታደሮች የፍተሻ ጣቢያ በጣሱ የተባበሩት መንግሥታት ሠራተኞች ላይ እንደተኮሱና በቁጥጥር ስር እንዳዋሏቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ፍሰት ቃል አቀባይ አምባሳደር ሬድዋን አረጋገጡ።

የመንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኞች ባለፈው ሳምንት እሁድ ኅዳር 27/2013 ዓ.ም የኤርትራ ስደተኞች የሚገኙበትን ማዕከልን ለመጎብኘት ሲያቀኑ የነበሩና ፍተሻ ጣቢያዎችን ጥሰው አልፈዋል ተብሏል።

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እንዳሉት የድርጅቱ ሠራተኞ መሄድ ወዳልተፈቀደላቸው አካባቢ በመግባት የመንግሥትን መመሪያ በመተለለፋቸው ነው የተተኮሰባቸውና የተያዙት።

"የተወሰኑ የተባበሩት መንግሥታት ሠራተኞች በቁጥጥር ስር ውለዋል የተተኮሰባቸውም አሉ" ማለታቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።

"ሁለት የፍተሻ ጣቢያዎችን በመጣስ ነድተው ነው ያልተፈቀደላቸው ቦታ የገቡት። እንዳይሄዱም ተነግሯቸዋል። ሦስተኛውን የፍተሻ ጣቢያም ሊጥሱ ሲሉ ነው የተተኮሰባቸው እንዲሁም በቁጥጥር ስር የዋሉት" በማለት ሬድዋን መናገራቸውን ኤኤፍፒ በዘገባው አመልክቷል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስለ ክስተቱ ምንም አይነት አስተያየት አልሰጠም።

ሮይተርስም በዘገባው የተባበሩት መንግሥታት በፀጥታ አባላት ባለፈው ሳምንት እሁድ የተተኮሰባቸው ሠራተኞች ሽመልባ የተባለውን የኤርትራ ስደተኞች ማዕከል ሊጎበኙ የነበሩና ሁለት የፍተሻ ጣቢያዎችም ላይ ሳያቆሙ ጥሰው ሄደዋል ብሏል።

ቡድኑ በአካባቢው እርዳታ ለማቅረብ የመንገዶችን ሁኔታ ለመገምገም የተላኩ አራት አባላትን ይዟል በማለትም ሮይተርስ የተባበሩት መንግሥታት ቃለ አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

በፌደራል መንግሥትና በህወሓት መካከል ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የተቀሰቀሰው ወታደራዊ ግጭት መቋጫ አላገኘም።

በክልሉም የኤርትራ ስደተኞች ጉዳይ አሳሳቢም እንደሆነም እየተገለፀ ነው። በተለይም ያልተረጋገጡ ቢሆኑም የኤርትራ ወታደሮች ወደ ትግራይ ገብተው ስደተኞቹን ወደ ኤርትራ እየመለሷቸው ነው የሚሉ ሪፖርቶች መውጣታቸውም ስጋትን አጭረዋል።

የኢትዮጵያም ሆነ የኤርትራ መንግሥታት የኤርትራ ወታደሮች ህወሓትን ለመውጋት ተሳትፈዋል የሚባለውን አይቀበሉትም።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦትን ለማድረስ አስተማማኝ መተላለፊያ መንገድ ሊመቻች ይገባልም እያለ ነው።

የእርዳታ ድርጅቶች ከስምንት ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ባሏት ትግራይ ክልል የምግብና የህክምና ቁሳቁሶች ግብአት እጥረትም አጋጥሟል እያሉ ነው።

በኢትዮጵያ ያሉ የስደተኞች ሁኔታ

በኤርትራ ያለውን አስገዳጅ ብሔራዊ ውትድርናና ፖለቲካዊ ጭቆና ለማምለጥ በርካታ ኤርትራውያን ስደተኞች ድንበር አቋርጠው ወደ ትግራይ ክልል ገብተዋል።

ኤርትራ ነፃነቷን ካገኘችበት ጀምሮ በአንድ ፓርቲ ስር በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እየተመራች ያለች አገር ናት።

በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ ሁለቱ አገራት ሰላምና ጦርነት በሌለበት ሁኔታ ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል ተፋጥጠው ነበር።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይና በፕሬዚዳንት ኢሳያስ የተደረገውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ፍጥጫውም የቆመ ሲሆን ለዚሁ ተግባራቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይም የኖቤል ሽልማት ማግኘታቸው ይታወሳል።

ሆኖም በሁለቱ መሪዎች መካከል የተደረሰው ስምምነት ግን "ወታደራዊ ትብብር" ሆኗል በማለት እየተቹ ሲሆን ለዚህም የሚያቀርቡት በሺዎች የሚቆጠሩ የኤርትራ ወታደሮች ህወሓትን ለመውጋት ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል የሚል ነው።

ሁለቱም መንግሥታት የኤርትራ ሰራዊት በጦርነቱ መሳተፉን ቢክዱም የሮይተርስ ዜና አገልግሎት የአሜሪካ መንግሥትን ምንጭ በመጥቀስ የኤርትራ ኃይል በትግራይ ውጊያ መሳተፋቸውን ማረጋጋጣቸውን ዘግቧል።

"በዚህ ጉዳይ ምንም መጠራጠር የለም" በማለት ስማቸው ያልተጠቀሰው ምንጭ መናገራቸውን ሮይተርስ አስነብቧል።

ከዚሀም በተጨማሪ ግጭቱ ከተጀመረ በኋላ ህወሃት ወደ ኤርትራ ሮኬቶችን አስወንጭፏል።

ወታደራዊው ውጊያ ተቋጭቷል?

የመከላከያ ሠራዊት የትግራይ ክልል መቀመጫን መቀለን ህዳር 19/2013 ዓ.ም ቢቆጣጠርም ውጊያዎች ግን በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ ሌሎች ምንጮች ይጠቁማሉ።

ለዚህም "ያልተቆጣጠርናቸው የቀሩ የሚሊሺያ ወይም የልዩ ኃይል አባላት አሉ" በማለትም አምባሳደር ሬድዋን ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ስልጣን ላይ መምጣታቸውን ተከትሎ በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው ግንኙነት እየሻከረ የመጣ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጓቸው ማሻሻያዎችም ላይ ልዩነቶች የነበሯቸው ሲሆን ኋላ ላይ እጅጉን ተካሮ ቆይቶ ነበር።

ይህንንም ተከትሎ በትግራይ ክልል ከአንድ ወር በፊት የተቀሰቀሰው ወታደራዊ ግጭት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የትግራይ ልዩ ኃይል በክልሉ የሚገኘውን የመከላከያ ሰሜን ዕዝ ካምፕ ላይ ጥቃት ማድረሱን ከገለጹ በኋላ መሆኑ ይታወሳል።

በዚህ ግጭትም ከ40 ሺህ በላይ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ድንበር አቋርጠው ወደ ሱዳን የተሰደዱ ሲሆን በርካቶችም እንዲሁ ከቤታቸው መፈናቀላቸው ተነግሯል።