ትግራይ፡ የኤርትራ መንግሥት በጦርነቱ በቀጥታ ተሳትፏል ሲሉ የክልሉ ፕሬዝዳንት ከሰሱ

ዶክተር ደብረጽዮን

በትግራይ ክልልና በፌደራል መንግሥት መካከል አየተካሄደ ባለው ግጭት ውስጥ የኤርትራ መንግሥት በቀጥታ ተሳታፊ ሆኗል ሲሉ የትግራይ ርዕሰ መስተዳድር ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ተናገሩ።

የኤርትራና የኢትዮጵያ መንግሥታት ግን በትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት በኩል የቀረበውን ክስ ሐሰት ነው ሲሉ አጣጥለውታል።

ፕሬዚዳንቱ በዛሬው ዕለት ህዳር 1/2013 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ የኤርትራ ሠራዊት አባላት በምዕራብ ትግራይ በኩል ከፍተኛ ድብደባ ፈፅመዋል ሲሉ ከሰዋል።

"በትናንትናው ዕለት የኤርትራ ሠራዊት አባላት ከፌደራል መንግሥት ጋር በመወገን በሁመራ በካባድ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት ፈፅመዋል" ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የኤርትራ ሠራዊት አባላት በዛሬው ዕለት ድንበር ጥሰው በባድመ በኩል በመግባት ጦርነት ከፍተዋልም ሲሉ በመግለጫቸው ላይ ያከሉት ደብረፅዮን የኤርትራ መንግሥት በጦርነቱ ተሳታፊ መሆን፣ ጦርነቱን "ወደተለየ ምዕራፍ አሸጋግሮታል" ብለዋል።።

"አሁንም ተመልሰን ወደዚህ ጦርነት መግባታችን ያሳዝናል። ባለፈው ይብቃ- ብለን ነበር። ወደ ሌላ ምዕራፍ ተሸጋግረናል። ትግራይ ላይ ትልቅ ክህደት ተፈጽሞባታል" ብለዋል።

"ኤርትራውያን ይሄ ሁኔታ እንዳይፈጠር ብዙ ጥረት አድርጋችኋል። አመስግነናል። አሁንም እናመሰግናለን። ይሁን እንጂ ኢሳይያስ ከዐብይና ከአሃዳዊ ኃይሎች ጋር በመወገን የጀመርነውን ራሳችንን የመከላከል ዘመቻ ሊያከሽፍ መጥቷል። ይህንን ያደረገው በጦርነቱ የኛን የበላይነት አይቶ ነው" በማለትም ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ በጦርነቱ የኤርትራ ሠራዊት አባልት በቀጥታ ተሳትፈዋል ስለመባሉ ቢቢሲ ከገለልተኛ አካል ማረጋገጥ አልቻለም።

ሆኖም የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳሌህ ይህንን የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንትን ክስ ማጣጣላቸውን ሮይተርስ በዘገባው አመልክቷል።

"ይሄ ውስጣዊ ግጭት ነው። እና የግጭቱ አካል አይደለንም" ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በስልክ እንደገለጹለት ሮይተርስ ዘግቧል።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ሜጀር ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደተናገሩት በኤርትራ ወታደሮች ጥቃት ስለመፈጸሙ በደብረጺዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) የተሰጠው መግለጫ "ፍፁም ሐሰት" መሆኑን ተናግረዋል።

በተለያዩ አቅጣጫዎች ዘመቻ እያካሄደ የሚገኘው የፌደራል መንግሥት ሠራዊት በምዕራብ የሚገኘውን የሁመራ አየር ማረፊያን መቆጣጠሩን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዛሬ [ማክሰኞ] ጠዋት ዘግበዋል።

ከዚህም በተጨማሪም በአካባቢው የነበሩ የትግራይ ልዩ ኃይል፣ ፖሊስ እና ሚሊሻ አባላትም እጃቸውን ሰጥተዋል ብለዋል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሻከረ የመጣው የፌደራልና የትግራይ ክልል መንግሥት ግንኙነት የማይታረቅ ደረጃ ደርሶ ከሳምንት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የትግራይ ልዩ ኃይል በክልሉ የሚገኘውን የመከላከያ ሰሜን ዕዝ ካምፕ ላይ ጥቃት ማድረሱን ገልፀው ጦርነት መከፈቱን አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው የመከላከያ ሠራዊት በኮማንድ ፖስት እየተመራ "አገሩን የማዳን ተልዕኮውን እንዲወጣ ትዕዛዝ ተሰጥቶታል" ብለዋል።

የትግራይ ክልል በበኩሉ በክልሉ የሚገኙት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰሜን ዕዝ ሰራዊት አባላትና አዛዦች ከትግራይ ክልል መንግሥት ጎን ለመሰለፍ ወስነዋል ማለቱ ይታወሳል።