"ወታደራዊው ተልዕኮ ውስን ነው" ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ

የትግራይ ልዩ ኃይል የፌደራል ሰራዊቱን መለዮ ለብሶ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የፌደራል መንግሥቱ ትግራይ ክልል ላይ የሚያደርገው ወታደራዊ ዘመቻ "ግልፅ፣ ውስንና ተጨባጭ ውጤቶችን ማግኘት" ላይ ያነጣጠረ ነው ብለዋል።

የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) በበኩላቸው ከዚህ ቀደም የፌደራል አስተዳደሩ ክልሉን ለመውረር እያሴረ ነው በማለት ሲወነጅሉ ተሰምተዋል።

በፌደራል መንግሥቱና በክልሉ ያለው ወታደራዊ ግጭት ወደ እርስ በርስ ጦርነትም እንዳያመራም ስጋቶች አሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአስቸኳይ ጦርነቱን እንዲያረግቡትም ጥሪ አድርጓል።

ግጭቱ በምን ሁኔታ ነው ያለው?

የፌደራል መከላከያ ሰራዊት ወደ ትግራይ ክልል ተጨማሪ ወታደሮችን እንደሚልክና በአገሪቷም የሚገኙ የሰራዊቱ አባላትንም እየተሰበሰሰቡ መሆኑንም የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት ምክትል ኤታማዦር ሹም እና የኦፕሬሽን ዘርፍ ሐላፊ ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ከሰሞኑ አስታውቀዋል።

ጄኔራል ብርሃኑ እንዳሉት የሰራዊት አባላቱ በክልሉ ለሚገኘው የመከላከያ ሰሜን ዕዝ ድጋፍ ለመስጠት እንደሆነ ገልፀዋል። የሰሜን እዝ በክልሉ አስተዳዳሪ ህወሃት ቁጥጥር ስር እንዳለ ክልሉ ገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በትግራይ ላይ የሚደረገው የጦር ተልዕኮ "ውስን" እንደሆነና "የፌደራል መንግሥት ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ለወራት ያህል በትእግስት ተሞክሮ ባለመሳካቱ ጦርነቱም የመጨረሻ አማራጭ ሆኗል" በማለት በትዊተር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።

የ X ይዘትን ይለፉት, 1
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ፡ የሦስተኛ ወገን ይዘቶች ማስታወቂያ ሊኖራቸው ይችላል

የ X ይዘት መጨረሻ, 1

1px transparent line

የክልሉ ፕሬዚዳንት ደብረፅዮን በበኩላቸው የትግራይ ኃይል በክልሉ የሚገኙትን የመከላከያ ሰሜን ዕዝ ጦር መሳሪያም ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር አውሏል ብለዋል።

ቀውሱ እየተቀጣጠለና ምንም አይነት የመቀዛቀዝ ሁኔታም እንደሌለም እየተነገረ ነው።

በውጊያው ስለተገደሉም ሆነ ስለተጎዱ ሰዎች ምንም አይነት መረጃ ባለመገኘቱ ግጭቱ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ማወቁን ፈታኝ አድርጎታል።

ይህም በተወሰነ መንገድ ግጭቱን ተከትሎ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት በትግራይ ክልል ከመቋረጡ ጋር ተያያይዞ ነው። በክልሉ ተቋርጦ የነበረው የመብራት አገልግሎት በአሁኑ ወቅት ተመልሷል።

1px transparent line

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ስለ ግጭቱ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት የተቆጠቡ ሲሆን በምትኩ የጦርነት ተልዕኮው ሲጠናቀቅ መረጃዎች ይፋ እንደሚሆኑ ቃል ገብተዋል።

በአሁኑ ሰዓት የምናውቀው ነገር ቢኖር የጦርነት ወሬዎች ከሁለቱም አካላት በተደጋጋሚ መነገራቸውን ነው።

ደብረፅዮን በበኩላቸው ክልሉን ለመከላከል ዝግጁ እንደሆኑ ገልፀው ትግራይ "ለወራሪዎች መቀበሪያ ትሆናለች" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ህወሃት በተደጋጋሚ ግጭት በማነሳሳት የወነጀሉት ሲሆን "ቀዩ መሥመር የመጨረሻው ነጥብ ታልፏል።" ብለዋል።

ጄኔራል ብርሃኑ በበኩላቸው ለህወሃት ታማኝ የሆኑ የክልሉ የፀጥታ ኃይሎችንም በአገር ክህደት ወንጅለዋቸዋል።

የፌደራል መንግሥቱንና ክልሉን ምላሽ የተመለከቱ ታዛቢዎች የእርስ በርስ ጦርነት ጅማሮ ነው በማለት ቢሰጉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን ይህንን ፍራቻ ቀለል አድርገውታል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የወጣው መግለጫ እንደሚያመላክተው የትግራይ ክልል ለመጪዎቹ ስድስር ወራት በወታደራዊ ዕዝ (ኮማንድ ፖስት) ትተዳደራለች። በጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የሚመራም ግብረ ኃይል ተቋቁሟል።

ግብረ ኃይሉ፦

  • የክልሉን የፀጥታ ኃይል ትጥቅ እንዲፈቱ ማድረግ
  • የእንቅስቃሴ ገደብ መጣል
  • የሰዓት እላፊ ገደብ የማውጣት
  • ህገወጥ በሆነ ተግባር ተሳታፊ የሆኑና ህገ መንግሥታዊውን ስርአት አደጋ ውስጥ የሚከቱ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል እንዲሁም ተመጣጣኝ ኃይልን በመጠቀም ህግና ስርአት የማስፈን ስልጣን እንዳለውም ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት ጀምሮ የክልሉ አስተዳዳሪ ህወሃትና የፌደራል መንግሥት ግንኙነት ከጊዜ ወደጊዜ እየሻከረ መጥቶ የማይታረቅ የቅራኔ ደረጃም ላይ ደርሰዋል።

ለሁለት አስርት አመታት የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ መስራችና አውራ የነበረው ህወሃት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን በመጡ ማግስት ተፅእኖው ቀንሷል።

በባለፈው አመትም በብሄር የተደራጁትን የግንባሩን ፓርቲዎች በማዋሃድ ብሄራዊ የሆነ ብልፅግና ፓርቲን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢመሰርቱም ህወሃት አልቀላቀልም በማለት በእምቢተኝነት ፀንቷል።

በዛሬው ዕለት ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ በወጣው መግለጫው የተወሰኑ የህወሃት አባላት "ከፍትህ ሸሽተው" እንደተደበቁና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገሪቱ ላይ ያደረጉትን ማሻሻያ የሚቃወሙ ናቸው ብለዋል።

በተለይም የፌደራልና የትግራይ ክልል መንግሥት ግንኙነት የማይታረቅ ደረጃ የደረሰው በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ሆነ ፓርላማው ምርጫው በሕገ መንግሥት ትርጓሜ እንዲራዘም ያፀደቀ ቢሆንም የትግራይ ክልል ምርጫ ማድረጉ የበለጠ ነገሩን አክርሮታል።

የፌደራል መንግሥት ክልሉ ያደረገውን ምርጫ ህገወጥና ተፈፃሚነት የሌለው ነው ብሏል።

በፌደራል መንግሥቱ ተቀባይነት ሳይኖረው ክልሉ ያደረገው ምርጫ ጥያቄን የፈጠረ ሲሆን ክልሏ ራሷን የቻለ አስተዳደር 'ዲፋክቶ ስቴት' እንዲኖራት የሞከረ ነው በማለት አስተያየታቸውን የሰጡ አሉ።

ህወሃት በበኩሉ ክልሉ የኢትዮጵያ አካል እንደሆነና" የራስን በራስ መተዳዳርና የመወሰን መብትን" አሳልፎ እንደማይሰጥና ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ጠንካራ አሃዳዊ ስርአት" ለመገንባት እየሞከሩ ነው በማለት ተቃውሟል።

የፌደራል መንግሥት በትግራይ ላይ ለስድስት ወራት የሚቆይ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያሳለፈ ሲሆን በክልሉ በረራዎችን ማድረግም ተከልክሏል።

ዲፕሎማቶች ምን እያሉ ነው?

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በፌደራል መንግሥትና በትግራይ ክልል የተፈጠረው ግጭት "እጅግ አሳሳቢ" እንደሆነ ገልፀው ውጊያውን እንዲያረግቡት ጥሪ አድርገዋል።

የ X ይዘትን ይለፉት, 2
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ፡ የሦስተኛ ወገን ይዘቶች ማስታወቂያ ሊኖራቸው ይችላል

የ X ይዘት መጨረሻ, 2

በዚሁ ሳምንት በአሜሪካ ምርጫ ተሰቅዘው ያሉት የውጭ ጉዳይ ኃላፊው ማይክ ፖምፔዮም ግጭቱ እንዲቆም ጥሪ አድርገዋል።

"በዚህ ሁኔታ ህይወት መታጣቱ አሳዝኖራል። ሰላም እንዲመለስና ግጭቶች እንዲረግቡ አስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ እናደርጋለን። የሰላማዊ ዜጎች ደህንነትና ጥበቃ አስፈላጊ ነው" ብለዋል በመግለጫቸው

በአዲስ አበባ ተቀማጭነቱን ያደረገው የአፍሪካ ህብረትም በበኩሉ ውይይት እንዲካሄዱ ግፊት ቢያደርግም መንግሥት ለድርድር ፈቃደኛ እንዳልሆነ ሮይተርስ ምንጮችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።