በኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ለምን ይፈራል?

ትግራይ ክልል የተደረገው ምርጫ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የትግራይ ክልልና የፌደራል መንግሥት ወታደራዊ ግጭት ውስጥ ከገቡ ሶስተኛ ቀናቸውን አስቆጥረዋል። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጥሪ ቢያደርግም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት በትግራይ ክልል የሚያደርገውን ወታደራዊ ጥቃት ለመቀጠል ቃል ገብቷል፡፡

በአንድ ወቅት ኢትዮጵያን ሲያስተዳድር በነበረው ግንባር ውስጥ አውራ ፓርቲ በነበረው በህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) እና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) መካከል የተፈጠረው ውዝግብ ለወራት ሞቅ ቀዝቀዝ ሲል ቆይቶ ጫፍ የደረሰው ህወሃት የፌደራሉን መንግሥት በመቃወም ክልላዊ ምርጫ ካካሄደ በኋላ ነው።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሻከረ የመጣው የፌደራልና የትግራይ ክልል መንግሥት ግንኙነት የማይታረቅ ደረጃ የደረሰው በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ሆነ ፓርላማው ምርጫው በሕገ መንግሥት ትርጓሜ እንዲራዘም ያፀደቀ ቢሆንም የትግራይ ክልል ምርጫ ማድረጉ የበለጠ ነገሩን አክርሮታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በፌደራል ጦር ሰፈር ላይ በተፈፀመ ጥቃት "ብዙዎች ተሰውተው፣ የአካል ጉዳት እና የንብረት ውድመት" መከሰቱን ከተናገሩ በኋላ ወታደራዊ ኃይሉ በትግራይ ላይ ጥቃት እንዲሰነዝር አዘዙ ፡፡

ለዚህም የክልሉ ገዥ ፓርቲን ተጠያቂ አድርገዋል ፡፡

ውጥረቱ እንዴት መጣ?

የፌደራል መንግስት በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሃገራዊ ምርጫ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ መወሰኑንተከትሎ ባለፈው መስከረም በትግራይ ምርጫ መካሄዱ ለተፈጠረው ውጥረት መባባስ መንስኤ እንደሆነ ይወሰዳል፡፡

ሆኖም ውጥረቱ ረዘም ላለ ጊዜ እየጋለ ሲሄድ ነበር፡፡

ለአስርት ዓመታት በኢትዮጵያ አውራ የፖለቲካ ፓርቲ የነበረው ህወሃት ከሶስት አመት በፊት የዐብይ መንግስት ወደ ስልጣን መጥቶ ብዙም ሳይቆይ ነው ቅራኔ መፈጠር የጀመረው፡፡

"የለውጥ አራማጅ" የተባሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀደሙት መንግሥታት የነበሩትን ባለስልጣናት በሙስና እና በሰብአዊ መብት ጥሰቶች ከመክሰስ ባለፈ ቁልፍ የህወሃት ሰዎችን ከማዕከላዊ መንግስት አስወገዱ፡፡

ከእነዚህ መካከል አንዱ የሆኑት የቀድሞው የደህንነት ኃላፊ እና የህወሃት ከፍተኛ ባለስልጣን የነበሩት አቶ ጌታቸው አሰፋ ከእስር በመሸሽ ወደ ትግራይ የተሰደዱ ሲሆን አሁንም በሽሽት ላይ ይገኛሉ፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ባለፈው ዓመት ብሔርን መሠረት በማድረግ የተቋቋመውን እና ሃገሪቱን ሲያስተዳድር የነበረውን ኢህአዴግን በማፍረስ ብልጽግና ፓርቲን ለማቋቋም መወሰናቸው ውጥረቶቹ ላይ ነዳጅ ጨምሯል፡፡

ህወሃት ውሳኔው አገሪቱን ይከፋፍላል በማለት የተቃወመ ሲሆን ብልጽግናንም ለመቀላቀል ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል፡፡

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ምክንያት በማድረግ የፌዴራሉ መንግስት ባለፈው ዓመት መጨረሻ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደውን ምርጫ ለሌላ ጊዜ ካስተላለፈ በኋላ አለመግባባቱ ይበልጥ እየሰፋ ሄደ፡፡

በትግራይ ክልል ምርጫ ለማካሄድ መወሰኑ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በፌዴራል መንግሥት ላይ የተደረገ የእምቢተኛ ድርጊት ነበር፡፡ የፌዴራሉ ፓርላማ ምርጫውን "ህገ ወጥ" ብሎታል፡፡

ከዚያን ጀምሮ ሁለቱም መንግሥታት አንዳቸው ሌላኛውን "ሕገ ወጥና ኢ-ሕገ መንግሥታዊ" ብለው ሲፈርጁ ቆይተዋል፡፡

የመቀሌ ነዋሪ በፈረስ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ህወሃት ከዚህ በፊት በፌደራል ህገ-መንግስት ውስጥ "የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትን" የሚፈቅደውን አንቀፅ በመጥቀስ እንደሚገነጠል ዲፋክቶ ስቴት እንደሚያቋቁም ሲዝት ነበር፡፡

ደብረፅዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ነሐሴ ወር ላይ እንደተናገሩት "በከፍተኛ ትግል ያገኘነውን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እና በራስ የመመራት መብታችንን ለማፈን ለሚፈልግ ለማንም ወደ ኋላ አንልም" ብለዋል፡፡

በጥቅምት ወር ደግሞ የፌደራል መንግሥት ከትግራይ ክልል ምክር ቤትና ከፍተኛ የሕግ አስፈፃሚ አካላት ጋር ምንም ግንኙነት ላለማድረግም የወሰነ ሲሆን ፓርላማውም ለትግራይ የሚሰጠውን የበጀት ድጎማ እንዳይደረግም አግዷል።

የህወሃት ወሳኝነት ሚና

ግንቦት 20/1983 ዓ.ም የቀድሞው ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ እና እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ ሕወሃት የፓርቲዎች ስብስብ በነበረው ገዢ ግንባር ውስጥ አውራ ከመሆኑም በላይ ትግራይንም እያስተዳደረ ነው፡፡

መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን ከስልጣን በማስወገድ ህወሃት ወሳኝ ሚና ከመጫወት ባለፈ የአገሪቱን ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚውንም መቆጣጠር ቻለ፡፡

የህወሃት ከዐብይ መንግስት ጋር አለመግባባቱ በአገሪቱ ውስጥ ባለው የኃይል ክፍል ውስጥ ትልቅ ስብራት ሆኗል፡፡

ደብረፅዮንን ጨምሮ አብዛኛዎቹ የትግራይ ክልል አመራሮች ለረጅም ጊዜ በማዕከላዊ መንግሥት ውስጥ አገልግለዋል፡፡

አንጋፋው ታጋይ ደብረጽዮን በአንድ ወቅት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው እስከማገልገል ደርሰዋል፡፡ ጓዶቻቸው እና አማካሪዎቻቸው ዐብይ ወደ ስልጣን እስኪመጡ ድረስም በአገሪቱ ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎችን ይዘው ነበር፡፡

መንግሥቱ ኃይለማርያም ከፊደል ካስትሮ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የህወሃት ፍላጎት ምንድነው?

የትግራይ አስተዳደር የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ማሻሻያ አሁን ያለውን የፌዴራል አደረጃጀት የሚያፈርስ እና አሃዳዊ የመንግሥት ሥርዓትን ለመገንባት እንደሚደረግ ሙከራ አድርጎ ይመለከተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ያላቸውንም ወዳጅነት "መርህ አልባ" ነው ብሎ የሚጠራው።

ዐብይ ለረጅም ጊዜ እንደጠላት ከምትታየው ከኤርትራ ጋር ሠላምን ለማምጣት ባደረጉት ጥረት እ.ኤ.አ. በ 2019 የኖቤል የሰላም ሽልማትን አሸንፈዋል፡፡

ህወሃት ግን የትግራይ ፍላጎቶች ችላ እንደተባሉ እና ለወደፊቱም ቢሆን ከጎረቤት ሃገሯ ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት የበለጠ ተሳትፎ እንዲኖረው ይፈልጋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበኩላቸው የህወሃት ባለስልጣናት ስልጣናቸውን ዝቅ አድርገው እየተመለከቱ ነው ብለው ያምናሉ፡፡

ኤርትራ በትግራይ ግጭት ውስጥ ተሳታፊ ናት?

በህወሃት እና ከትግራይ ክልል ጋር ረዥም ድንበር በሚጋራው በኤርትራ መንግሥት መካከል ለዓመታት የዘለቀ አለመግባባት አለ።

ከ1990-1992 ባለው ጊዜ የተካሄደው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የተጀመረው በሁለቱ መካከል ባለው የድንበር ውዝግብ ሲሆን በተለይም ደግሞ በባድመ ከተማ ይገባኛል ምክንያት ነው።

የባድመ ሁኔታ እስካሁን እልባት ያላገኘ ሲሆን ኤርትራ በተባበሩት መንግሥታት በሚደገፈው የድንበር ኮሚሽን ውሳኔ መሠረት ኢትዮጵያ ከተማዋን አሳልፋ እንድትሰጣት ትፈልጋለች ፡፡

ነገር ግን ይህ አካባቢውን ከሚያስተዳድረው የትግራይ መንግሥት ትብብር ውጭ ሊሳካ የሚችል አይመስልም፡፡

የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ጽህፈት ቤት በፌዴራል ጦር ሰፈር ላይ ስለተፈፀመው ጥቃት ሲገልጽ ህወሃት የጎረቤት ሃገር የኤርትራን ጦር የሚመስል መለዮ ጦሩን በማልበስ "በትግራይ ህዝብ ላይ በኤርትራ መንግስት የተፈፀመ ጥቃት ነው የሚል ሃሰተኛ መረጃ ለመፍጠር ሞክሯል" ሲል ይወነጅላል፡፡

ይህ ክስ በሦስተኛ ወገን ባይረጋገጥም ኤርትራ በትግራይ ለተፈጠረው ቀውስ ምን ዓይነት ምላሽ እንደምትሰጥ እና ወደ ጎረቤቷ የውስጥ ጉዳይ ትገባ ይሆን የሚል ስጋት አስከትሏል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ወደ መጠነ ሰፊ ጦርነት ምን ያህል ሊሸጋገር ይችላል?

የትግራይ ክልል ርእሰ መስተዳድር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) "ለተቃዋሚዎች የቀብር ስፍራ" የሆነውን ክልል ለመከላከል መዘጋጀታቸውን ገልፀው የትግራይ ተወላጆች ሁኔታውን ተረድተው አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ሁሉ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

እንደ ደብረፅዮን ከሆነ "ሠራዊታችንን፣ ሚሊሻችንን እና ልዩ ኃይላችንን አዘጋጅተናል። ዝግጅታችን ጦርነትን ለማስወገድ ያለመ ቢሆንም ለመዋጋት ካስፈለገንም ለማሸነፍ ዝግጁ ነን" ብለዋል ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጽሕፈት ቤት የወታደራዊ ፍጥጫውን ትክክለኛነት ለማሳየት ህወሃትን "የማያባራ አመጽ እየቀሰቀሰ ነው" ሲል የከሰሰው ሲሆን "የመጨረሻውን ቀይ መስመርም አልፏል" ብለዋል፡፡

እነዚህ ንግግሮች ችግር አላቸው።

በትግራይ ውስጥ ያለው ግጭት በሠላማዊ መንገድ ካልተፈታ በቀላሉ ሊፈነዳ የሚችል ሲሆን በተቀረው የአገሪቱ ክፍል በመዛመትም ውጥረቱን ሊያባብስ የሚችልባቸው አደጋዎች አሉ፡፡

በግጭቱ ያሉ ቁልፍ አካሎች

በፌደራል መንግሥትና በትግራይ ክልል መንግሥት ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ የኤርትና እና የሱዳንን ጉዳይ ማንሳት ይቻላል።

የትግራይ ክልልን በሰሜን ኤርትራ፣ በሰሜን ምዕራብ ደግሞ ሱዳን ያዋስናል።

ከጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ጋር ሽርክ የሆኑት ፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፤ ሕወሓት ለ1998ቱ የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ጦርነት ተጠያቂ ነው ብለው ያምናሉ።

የሱዳን ወታደራዊ መሪ ሌ/ጀነራል አብደልፈታህ አልቡርሀም ከሳምንት በፊት ለሁለት ቀናት ኢትዮጵያ ውስጥ ይፋዊ ጉብኝት አድርገው ነበር። ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር ጋር የሱዳን እና ኢትዮጵያን የድንበር ሰላም ለማስጠበቅ ተስማምተዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በትግራይ ክልል ስላለው ወታደራዊ ተልዕኮ አላማ ባይናገሩም፤ ወታደራዊ ኃይል በመጠቀም ሕወሓትን ከጨዋታ ውጪ የማድረግ እቅድ እንዳላቸው ግልጽ ነው።

በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ብሔር ተኮር ግጭቶች መቀስቀሳቸው ቀጥሏል።

የአንዳንድ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ እንደሚጠቁመው፤ በትግራይ ክልል የተከሰተው ግጭት ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ሊያመራ ይችላል።

ትግራይ ውስጥ ግጭት መነሳቱ፤ ውጥረት ውስጥ ካሉ እንደ ኦሮሚያ እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ያሉ አካባቢዎች መከላከያው ወደ ትግራይ እንዲያተኩር ያደርጋል። ይህም የደህንነት ስጋት ሊፈጥር ይችላል ተብሎ ይታመናል።

ግጭቱ ለጎረቤት አገር ኤርትራም ሊተርፍ ይችላል። የኤርትራ ተቃዋሚዎች ደጋፊ መስከረም ድረ ገጽ ጥቅምት 4 እንዳስነበበው፤ ኢሳያስ አፈወርቂ ስለ ትግራይ ጦርነት ከከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣኖች ጋር ተነጋግረዋል።

ግጭቱ 2018 ላይ የሰላም ስምምነት የተደረሰበት የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ክለላ ጉዳይን ሊያዘገይ ይችላል።

በትግራይ ክልል እና በፌደራል መንግሥት ግጭት የተነሳው ኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ከግብፅ ጋር ፍጥጫ ውስጥ ባለችበት ወቅትም ነው።