በትግራይና በፌደራል መንግሥት መካከል ስላለው ግጭት እስካሁን የምናውቀው

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድና ዶከተር ደብረፅዮን

የፎቶው ባለመብት, OFFICE OF THE PM

በትግራይ ክልል እና በፌደራል መንግሥት መካከል የነበረው መካረር ትላንት ምሽት ወደ ግጭት አምርቷል።

ትናንት ሌሊት (ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ. ም) ወደ አምስት ሰዓት አካባቢ በመቀሌና አስራ አንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ኩዊሃ ከፍተኛ የተኩስ ድምፅ ይሰማ እንደነበር የቢቢሲ ዘጋቢ ከስፍራው አድርሷል።

ቀጣዮቹ እስካሁን የምናውቃቸው ነጥቦች ናቸው።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ የሰጡት መግለጫ

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ዛሬ በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ቀርበው የአገር መከላከያ ሠራዊት በሕወሓት ላይ የኃይል እርምጃ እንዲወስድ ትዕዛዝ መሰጠቱን ተናግረዋል።

"ሕወሓት በትግራይ በሚገኘው የመከላከያ ካምፕ ላይ ጥቃት አድርሷል። ሰሜን ዕዝንም ለመዝረፍ ሙከራ አድርጓል" ብለዋል።

"ሕወሐት ግን እንደ ባዕድና እንደ ወራሪ አገር ሠራዊት ቆጥሮ፤ የመከላከያ ሠራዊቱን ለመምታትና ለመዝረፍ ተነሥቷል። በዳልሻሕ በኩልም ጦርነት ከፍቷል" ብለዋል።

አክለውም "የመከላከያ ሠራዊታችን በኮማንድ ፖስት እየተመራ አገሩን የማዳን ተልዕኮውን እንዲወጣ ትዕዛዝ ተሰጥቶታል። ቀዩ መሥመር የመጨረሻው ነጥብ ታልፏል። ሀገርና ሕዝብ ለማዳን ሲባል ኃይል የመጨረሻው አማራጭ ሆኗል" በማለት ገልፀዋል።

የስልክ፣ ኢንተርኔት እና በረራ መቋረጥ

በትግራይ ክልል ከትናንት ሌሊት ጀምሮ የኢንተርኔትና የስልክ አገልግሎት መቋረጡ ተገልጿል። በኢንተርኔት ነፃነት ላይ የሚሰራው ኔት ብሎክስ የተሰኘው ድርጅትም፤ ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ ኢንተርኔትና የስልክ አገልግሎት መቋረጡን አስታውቋል።

ወደ መቀለ እና ጎንደር የሚደረጉ በረራዎች መቋረጣቸውም ታውቋል።

ቢቢሲ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድረ ገጽ ላይ ወደ ሁለቱ ከተሞች የሚካሄድ በረራ እንደሌለ ተመልክቷል።

የትግራይ ክልል በሰጠው መግለጫም ወደ ክልሉ ማንኛውም በረራ እንደማይካሄድ አስታውቋል።

የአማራ ክልል ምን አለ?

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ትናንት ምሽት 4፡30 ጀምሮ በአጠቃላይ በሰሜን እዝ የመከላከያ ሠራዊት ካምፖች፣ ዴፖዎች፣ እና የተለያዩ መሰረተ ልማት ባሉባቸው አካባቢዎች ላይ የትግራይ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ፣ የተቀናጀ ጥቃት ማድረስ መጀመሩን በዛሬው ዕለት ለአማራ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

የትግራይ ክልል ልዩ ኃይል በክልሉ የሚገኘው የመከላከያ ኃይል አዛዦች እንዳይንቀሳቀስ ከማድረግ ጀምሮ አሁን ደግሞ ወደጥቃት መሸጋገሩን ተናግረዋል።

ሠራዊቱ ያለውን ትጥቅ ወደ መቀማት ሄዶ እንደነበርም አቶ ተመስገን አስታውቀዋል።

አቶ ተመስገን አክለውም በአማራ ክልልም ሶሮቃ እና ቅራቅር በሚባሉ አካባቢዎች የጥቃት ሙከራ ማድረጉንና በክልሉ ልዩ ኃይል መመከቱን ተናግረዋል።

የትግራይ ክልል የሰጠው መግለጫ

የትግራይ ክልል ዛሬ ባወጣው መግለጫ በክልሉ የሚገኙት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰሜን ዕዝ ሰራዊት አባላትና አዛዦች ከትግራይ ክልል መንግሥት ጎን ለመሰለፍ መወሰናቸውን አሳውቋል።

የትግራይ ክልል መንግሥት የተፈጠሩት የፖለቲካ ልዩነቶች በውይይት እንዲፈቱ በተደጋጋሚ ጥሪ ቢያቀርብም የተሰጠው "እንደ ሕዝብ ቅጣት ነው" በማለትም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰሜን ዕዝ ሰራዊትና አባላት ከትግራይ ክልል መንግሥት ጎን በመቆም አብረው መታገል መጀመራቸውን ገልጿል።

መግለጫው ከዛሬዋ እለት ጀምሮ ጥቅትም 25/ 2013 ዓ.ም በትግራይ ክልል ውስጥና ድንበር አካባቢ ማንኛውም ወታደራዊ እንቅስቃሴ የተከለከለ እንደሆነ ያትታል።

በተጨማሪም ወደ ትግራይ ክልል የሚደረግ ማንኛውም በረራ እንዳማይኖር የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ማድረግ እንደማይቻል ተገልጿል።

ይህንን ውሳኔ በመጣስ በሕዝብ ላይ ጉዳት ለማድረስ የሚወሰድ እርምጃ ተመጣጣኝ እርምጃ እንደሚወስድም አስጠንቅቋል።።

ለሌሎች የሰራዊት አባላት እና አዛዦችም ከሰሜን እዝ ሰራዊትና አዛዦች ጎን በመቆም ታሪካዊ ኃላፊነታቸውነ እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል።

በትግራይ ውስጥ ማንኛውም የትራንስፖርት አገልግሎትም እንደማይኖር በተጨማሪ ተገልጿል።

የፌደራል ፖሊስ የሰጠው ጥቆማ

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በአዲስ አበባ አስር ክፍለ ከተሞች የጸጥታ ችግርም ሆነ ማንኛውም አይነት እንቅስቃሴ በተመለከተ መረጃ መስጠት የሚቻልባቸው ስልክ ቁጥሮች አስታውቋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በትግራይ ክልል ለስድስት ወር የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል።

ምክር ቤቱ ዛሬ፣ ጥቅምት 25/2013 ባደረገው አስቸኳይ ልዩ ስብሰባ መንግሥት በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 93/1/ሀ መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉን አስታውቋል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት መግለጫ አክሎም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለስድስት ወራት ተፈጻሚ እንደሚሆን አስታውቆ ይህንን አዋጅ የሚያስፈፅም በኢፌድሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሰብሳቢነት የሚመራና አግባብነት ካላቸው አካላት የተወጣጡ አባላት ያሉት ግብረኃይል መቋቋሙን ገልጿል።

ግብረኃ ይሉ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲሆን "የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግብረሀይል" ተብሎ ይጠራልም ተብሏል።

ዩኒቨርስቲዎች የተማሪ ቅበላ ማራዘማቸው

በአገሪቱ የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ክልላዊ መንግሥት መካከል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት የተማሪዎችን ቅበላን ላልተወሰነ ጊዜ አራዝመዋል።

ተማሪዎችን ላልተወሰነ ጊዜ እንደማይቀበሉ ካስታወቁት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አምቦ፣ ባህር ዳር ፣ ደብረ ማርቆስና ወራቤ ዩኒቨርሲቲዎች ተጠቃሽ ናቸው።