የአማራ ክልል መንግሥት በድንበር አካባቢ ስላለው ግጭት ምን አለ?

የፎቶው ባለመብት, AMMA
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ትናንት ምሽት 4፡30 ጀምሮ በአጠቃላይ በሰሜን እዝ የመከላከያ ሠራዊት ካምፖች፣ ዴፖዎች፣ እና የተለያዩ መሰረተ ልማት ባሉባቸው አካባቢዎች ላይ የትግራይ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ፣ የተቀናጀ ጥቃት ማድረስ መጀመሩን በዛሬው ዕለት ለአማራ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
የትግራይ ክልል ልዩ ኃይል በክልሉ የሚገኘው የመከላከያ ኃይል አዛዦች እንዳይንቀሳቀስ ከማድረግ ጀምሮ አሁን ደግሞ ወደጥቃት መሸጋገሩን ተናግረዋል።
ሠራዊቱ ያለውን ትጥቅ ወደ መቀማት ሄዶ እንደነበርም አቶ ተመስገን አስታውቀዋል።
አቶ ተመስገን አክለውም በአማራ ክልልም ሶሮቃ እና ቅራቅር በሚባሉ አካባቢዎች የጥቃት ሙከራ ማድረጉንና በክልሉ ልዩ ኃይል መመከቱን ተናግረዋል።
እንደ አቶ ተመስገን ገለጻ ከሆነ በሌሎች የክልሉ አካባቢዎችም ሊገመት የሚችል ጥቃት ያለ ሲሆን፣ የክልሉ ልዩ ኃይል አንዳንድ በትግራይ ልዩ ኃይልና ሚኒሻ አባላት ከበባ ውስጥ የነበሩ የመከላከያ አባላትንም ማዳንና ማውጣት ችሏል ብለዋል።
ልዩ ኃይሉ ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ የከባድ መሳሪያዎችንም ከስፍራው በማውጣት ተመልሰው ለውጊያ እንዲዘጋጁ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
የኮማንድ ፖስቱን ከመከላከያ ጋር በመሆን በቅንጅት እየመሩና እየሰሩ መሆኑን የተናገሩት አቶ ተመስገን "የአማራ ሕዝብ ስትራቴጂካዊ ጠላቱን እስካላጠፋ ድረስ በየጊዜው የሸረሪት ድር ስናፀዳ አንኖርም" ብለዋል።
በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶች በሕወሓት የገንዘብ፣ የቁሳቁስ እና የሥልጠና ድጋፍ የሚደረግለት ነው በማለትም በአልመዳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ውስጥ የኤርትራ ወታደርን አይነት ልብሶችን በመስፋትና የትግራይን ልዩ ሀይል በማልበስ ለትግራይ ህዝብ ኤርትራ ወረረችህ በማለት ህዝቡን ሊያደናግር ነው በማለት ገልፀዋል።
ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይህንን ኃይል ሥርዓት የማስያዝ ስራ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በመሆን የክልሉ መንግሥት እንደሚሰራም ተናግረዋል።
ሁሉም የፀጥታ ኃይል የሚሰጠውን ትዕዛዝ ተቀብሎ የሚመጣውን ጥቃት ለመከላከል ዝግጁ እንዲሆን ተናግረዋል።
የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ከክልሉ መንግሥት እና ከፌደራል መንግሥቱ ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።
ከሰራዊቱ በተለያዩ ምክንያት ወጥተው የነበሩ አባላትም የክልሉ መንግሥት ጥሪ ማቅረቡን ተናግረዋል።












