የአፍሪካ ሕብረት፡ "ሁሉም አካል ግጭትን ከሚያባብስ ትርክት ይቆጠብ"

የኦሮሚያ ፖሊስ ከትናንት በስቲያ በምዕራብ ወለጋ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር 32 ነው ሲል የዓይን እማኞች እና አምነስቲ የሟቾች ቁጥር ቢያንስ 54 ነው ብለዋል።
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ ለብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ እሁድ ዕለት በደረሰው ጥቃት የተገደሉት ንጹሃን ዜጎች ቁጥር 32 ነው ብለዋል።
የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በበኩሉ በጥቃቱ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር 32 እንደሆነ ቢጠቀስም ኮሚሽኑ ያገኛቸው መረጃዎች አሃዙ ከዛ በላይ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማሉ ብሏል።
በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ጉሊሶ ወረዳ፣ ጋዋ ቃንቃ ቀበሌ በሰላማዊ ዜጎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት የሰዎች ሕይወት ማለፉን ይታወሳል።
የክልሉ ቃል አቀባይ ጥቃቱ የተፈጸመው በስብሰባ ስም በአንድ ቦታ በተሰበሰቡ ሰዎች ላይ ነው ብሏል።
የክልሉ መንግሥት ትናንት ባወጣው መግለጫ ምን ያክል ሰዎች በጥቃቱ እንደተገደሉ ያለው ነገር የለም።
የአፍሪካ ሕብረት፣ አምንስቲ ኢንተርናሽናልና ሌሎችም ድርጅቶች ጥቃቱን በማውገዝ መግለጫ አውጥተዋል።
"የ54 ሰው አስክሬን ተመልክቻለሁ"
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዓይን እማኞች ከ50 ያላነሱ ሰዎች መገደላቸውን ይናገራሉ።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ጥቃቱ የተፈጸመበት ቀበሌ ነዋሪ ጥቃቱ የተጀመረው ከቅዳሜ ዕለት ጀምሮ ነው ይላሉ።
"ልክ መከላከለያ እንደወጣ ኦነግ ሸኔ ገባ። ከዚያ ወረራ ጀመረ፤ ዘረፋ ጀመረ። ቅዳሜ ዕለት እንደዛ እያደረጉ አደሩ። ሞባይል ስልክ፣ ገንዘብ እንዲሁም የቤት እቃ ሲዘርፉ ነበር። ከዚያ ትላንት [እሁድ] 11 ሰዓት አካባቢ ስብሰባ አለ ብለው አዛውንት፣ ሴቶችና ሕፃናት ሳይለዩ ሰብስበው አንድ ትምህርት ቤት አስገቡ። ከዚያ ጥቃት ፈፀሙ።" ይላሉ።
የዓይኑ እማኙ ስብሰባውን የጠራው ጥቃት ያደረሰብን ኦነግ ሸኔ ነው ይላሉ።
"ሰዉ በፍርሃት ተገዶ ነው ወደ ስብሰባው የገባው። ሕይወቱ የሚተርፍ መስሎት ነው የሄደው። ከዚያ በመትረየስና በቦንብ ነው ጥቃት የፈፀሙት።"
የዓይኑ እማኙ ጥቃቱ ሲፈፀም ከሌሎች ሰዎች ጋር ሸሽተው ጫካ ውስጥ ተደብቀው እንደነበር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"የሚፈልጉት ወንዶችን ነበር። እኛ ሸሽተን ጫካ ውስጥ ነበርን። ሴቶች፣ ሽማግሌዎች ቤት ቀርተው ነበር። ገንዘብ ቢውስዱ እንጂ እነሱን አይነኩም ብለን ነበር ያሰብነው። ከዚያ የፍንዳታ ድምፅ ስንሰማ ቀስ ብለን ከተደበቅንበት ጫካ ወጥተን ስናይ አመድ ሆነዋል።"
ለደህንነታቸው በመስጋት ማንነታቸው እንዲገለፅ ያልፈቀዱት እኒህ የዓይን እማኝ ከሌሎች ሰዎች ጋር ጫካ ውስጥ አድረው ዛሬ [ሰኞ] ረፋዱን መውጣታቸውን ይናገራሉ።
ሰኞ ከረፈደ በኋላ ነው መከላከያና ልዩ ኃይል የገባልን ይላሉ።
ለቢቢሲ ቃላቸውን የሰጡት የዓይን እማኝ በስፋራው የነበረው የመከላከያ ሠራዊት ቅዳሜ ጠዋት አካባቢውን ለቆ እንደወጣ ይናገራሉ። መከላከያ ሠራዊት ሥፍራውን ለቆ በወጣ በሰዓታት ልዩነት ታጣቂዎች አከባቢውን እንደተቆጣጠሩ አስረድተዋል።
የምዕራብ ወለጋ ኮማንድ ፖስት ከታወጀ ወዲህ መከላከያ በሥፍራው እንደነበርም ያወሳሉ።
"አንድ ወንድሜ ሞቷል። የአጎቴ ልጅና አባቱ ሞተዋል። ወንድሜ ሚስትና ልጆች አሉት። አጎቴ ደግሞ ሽማግሌ ነበር። ወንድሜ ስብሰባ ሲጠራ ልጆቼን ልይ ብሎ ከጫካ ወጥቶ ሄዶ ነው የሞተው። ሚስትና ልጆቹም አብረው አለቁ።"
አሁን መከላከያ ከገባ ወዲህ በሥፍራው መረጋጋት እንዳለ የዓይን እማኙ ያስረዳሉ። መከላከያ ሠራዊት የሸሹትን እየጠራ እንደሆነና የሞቱ ሰዎችን ሬሳ እየሰበሰበ እንዳለ ይናገራሉ።
የዓይኑ እማኙ እስካሁን ድረስ 54 ሰዎች መሞታቸውን ማረጋገጣቸውን ይናገራሉ።
ሌላ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዓይን እማኝም ጥቃቱ የደረሰው ሰዎች በተሰበሰቡበት እንደሆነ ይናገራሉ።
"ጥሩ ነገር እንነግራችኋለን ብለው ከሰበሰቧቸው በኋላ ቦምብ ሲጥሉባቸው 60 ሰው ሕይወቱ አለፈ። 20 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል። የሰዎች አስክሬን አሁን እየተሰበሰበ ነው" ብለዋል።
እኚሁ የዓይን እማኝ ወደ አከባቢው የመንግሥት ጸጥታ ኃይል መሰማራቱን ተከትሎ ወደ ቀያቸው እየተመለሱ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የክልሉ መንግሥት ምላሽ
የኦሮሚያ ክልል ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ባልቻ ኦነግ ሸኔ የተባለው ቡድን ንሑሃን ዜጎችን ስብሰባ ብሎ ከጠራ በኋላ ሰዎች ላይ በተወረወረ ቦምብ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።
ጥቃቱ የተፈጸመው ከምሽቱ 12 ሰዓት አካባቢ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ጌታቸው፤ "ቦምቡን የወረወሩት ሐሰተኛ ስበሰባ የጠሩት ናቸው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ እየተጠቀሰ ነው። ነገር ግን ትክክለኛውን ቁጥር ለማወቅ በአካባቢው ያለው አካል አጣርቶ እስኪልክልን እየተጠባበቅን ነው" ይላሉ።
በተመሳሳይ የኦሮሚያ ክልል ዛሬ ንጋት ላይ መግለጫ አውጥቷል። ክልሉ "ጭካኔ በተሞላበት መንገድ የሰዎች ሕይወት እንዲያልፍ ባደረገው የኦነግ ሸኔ ቡድን ላይ እርምጃ ይወሰዳል" ብሏል።
የክልሉ ፕሬዝደንት አቶ ሽመልስ አብዲሳም በዜጎች ላይ ለደረሰው ጥቃት "ጥልቅ ሃዘኔን እገልጽለሁ" ያሉ ሲሆን "በኦነግ ሸኔ አሸባሪ ቡድን ላይ እየተወሰደ ያለው ውጤታማ እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ላረጋግጥ እወዳለሁ" ብለዋል።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ በበኩሉ ትላንት ምሽት የተፈጸመው ጥቃት መጠን እና ዝርዝር ሁኔታዎችን ከፌደራልና ከክልሉ መንግሥት ጋር በመተባበር እየተጠራ ነው ብሏል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ማንነትን መሠረት ባደረጉ ጥቃቶች ማዘናቸው በፌስቡክ ገፃቸው ገልፀዋል።
"የኢትዮጵያ ጠላቶች፤ "ወይ እኛ እንገዛለን፤ ወይ ሀገር አትኖርም" ብለው ተነሥተዋል። ለዚህም የጥፋት ዐቅማቸውን ሁሉ እየተጠቀሙ ነው። አንደኛው ዒላማቸውም የሕዝባችንን ቅስም መስበር ነው" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
"ግራ ቀኝ የሚያውቁ ሰዎችን እየሰበሰቡ በማሠልጠንና በማስታጠቅ በየአካባቢው ማንነትን መሠረት ያደረገ አረመኔያዊ ጥቃት ማድረስ" ጠላቶች ያሏቸው ሰዎች አላማ ነው ሲሉ በመግለጫቸው አትተዋል።
"መንግሥት በተለያዩ ቦታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ ያላቸውን ጥፋቶች በቅድሚያ መረጃ ሰብስቦ ርምጃ በመውሰድ ሲያከሽፍ ቆይቷል። ነገር ግን ያለፈው ሥርዓት ያወረሰንን ቀዳዳዎች ሁሉ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ደፍኖ መጨረስ አልተቻለም" ይላል የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ኦፊሴላዊ ገፅ ላይ የሰፈረው መልዕክት።
አክለውም "የጸጥታ አካላት ጥቃቱ ወደተፈጸመበት አካባቢ ተሠማርተዋል። ርምጃም እየወሰዱ ነው። በቀጣይም የሕዝባችንን ደኅንነት ለማስጠበቅ መንግሥት የመንግሥትነቱን ሥራ በቁርጥና በጽናት ይሠራል" ብለዋል።
የአፍሪካ ሕብረት
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሞሳ ፋኪ ማሕማት፤ ንጹሀን ዜጎች መገደላቸውን አጥብቀው እንደሚያወግዙ ገልጸዋል።
ሕብረቱ ባወጣው መግለጫ፤ መንግሥት ጥቃቱን የፈጸሙ ቡድኖችን ተጠያቂ ማድረግ እንዳለበት አሳስቧል።
በማኅበረሰቡ መካከል የሚከሰት ግጭት እየተባባሰ መምጣቱን በመጥቀስ፤ ሁሉም አካል ግጭትን ከሚያባብስ ትርክት እንዲቆጠብ ሊቀ መንበሩ ጠይቀዋል።
በአገሪቱ ግጭትን ለማርገብ ጥረት መደረግ እንዳለበት፣ ሁሉን አቀፍና ወደ ብሔራዊ መግባባት የሚወስድ የፖለቲከኞች ውይይት መካሄድ እንደሚገባውም መግለጫው ይጠቁማል።
ይህ ካልሆነ ግን አለመረጋጋቱ ከኢትዮጵያ አልፎ ለቀጠናውም ይተርፋል ያሉት ሊቀ መንበሩ፤ የአፍሪካ ሕብረት በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋትን እንዲሰፍን እንደሚያግዝም ገልጸዋል።
አምነስቲ
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከ54 የማያንሱ ብሄራቸው አማራ የሆኑ ሰዎች ተገድለዋል ብሏል ትናንት ባወጣው መግለጫ።
አምነስቲ የአገር መከላከያ አከባቢውን ጥሎ መውጣቱን ተከትሎ የኦሮሞ ነጻነት ጦር አባላት ሳይሆኑ እንደማይቀሩ የተጠረጠሩ ጥቃቱን መፈጸማቸውን ገልጿል።
መከላከያ ሠራዊት አከባቢውን ለምንና አንዴት ጥሎ መውጣት እንዳስፈለገው መጣራት ይገባዋል ብሏል አምነስቲ።
በጥቃቱ ሴቶች እና ሕጻናት ጭምር መገደላቸውን አምነስቲ በሪፖርቱ አመልክቷል።
የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በምዕራብ ወለጋ የተፈጸመውን ጥቃት አውግዟል። ኮሚሽኑ ወደ 60 የሚጠጉ ታጣቂዎች በሶስት ቀበሌዎች በሚኖሩ ብሄራቸው አማራ የሆኑ ነዋሪዎች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን አስታውቋል።
ኮሚሽኑ በጥቃቱ ሴቶች እና ህጻናት መገደላቸውንም ገልጾ በጥቃቱ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር 32 እንደሆነ ቢጠቀስም፤ ኮሚሽኑ ያገኛቸው መረጃዎች አሃዙ ከዛ በላይ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማሉ ብሏል።













