የግማሽ ሚሊዮን ብር ሰዓት ለሠራተኞቻቸው የሸለሙት አለቃ ሥራ ለቀቁ

የአውስትራሊያ ፓስታ ቤት ኃላፊ ለአራት ሠራተኞቻቸው ዋጋው የከበደ ሰዓት በመሸለማቸው ምክንያት ሥራ ለቀዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአውስትራሊያ ፓስታ ቤት ኃላፊ ለአራት ሠራተኞቻቸው ዋጋው የከበደ ሰዓት በመሸለማቸው ምክንያት ሥራ ለቀዋል።

የብሔራዊ ፓስታ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ክሪስቲን ሆልጌት ከአውሮፓውያኑ 2017 ጀምሮ ድርጅቱን ሲያገለግሉ ነበር።

ነገር ግን ለአራት ሠራተኞቻቸው 20 ሺህ የአውስትራሊያ ዶላር [ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ] የሚያወጡ ሰዓቶች ለአራት ሠራተኞቻቸው በመሸለማቸው ምክንያት ነው ራሳቸውን ከሥልጣን ያገለሉት።

የሴትዬዋ ድርጊት የሕዝብን ንብረት ያለአግባብ ማባከን ነው ተብሏል።

ካርቲዬል የተሰኘውን ሰዓት በ2018 [በአውሮፓውያኑ] ነበር 'ጠንካራ ሠራተኞቼ ናቸው' ላሏቸው ባልደረቦች የሸለሙት።

የሃገሪቱ ፓርላማ ከሰሞኑ ይህን ጉዳይ መዞ ምርመራ እንዲደረግባቸው ወስኗል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን በወጪው 'እጅግ እንደተገረሙ' ተናግረዋል። አልፎም እንግሊዛዊቷ ሥራ አስኪያጅ ከኃላፊነቱ እንድትነሳ አዘዋል።

"በአውስትራሊያ ፓስት አግልግሎት ውስጥ ያለች እያንዳንዷ ዶላር የግብር ከፋዩ ናት። ወጪም ቢሆን ሕዝብን ያከበረ መሆን አለበት" ሲሉ ተደምጠዋል።

የአውስትራሊያ ፖስታ አግልግሎት ባለቤትነቱ የመንግሥቱ ይሁን እንጂ የሚተዳደረው በግል ነው።

ኃላፊዋ ሰኞ ዕለት ሥልጣናቸውን እንደለቀቁ አሳውቀዋል።

ሥራ አስኪያጇ 'ሠራተኞች ለጠንካራ ሥራቸው ሊመሰገኑ ይገባል' ሲሉ ድርጊታቸውን በተደጋጋሚ ተከላክለዋል።

ሽልማቱ የተሰጣቸው ሠራተኞች ለአውስትራሊያ ፖስታ አግልግሎት 220 ሚሊዪን የአውስትራሊያ ዶላር አምጥተዋል፤ ይህ ደግሞ የፋይናንስ አቅማችንን አጠናክሯል ብለዋል።

'ነገር ግን በ2018 የወሰንነው ውሳኔ እንዲህ ዓይነት ነገር መፍጠሩ ይፀፅተኛል' ሲሉ በመግለጫቸው አትተተዋል።

የአውስትራሊያ ፖስታ አገልግሎት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ምርትና አገልግሎት በማጓጓዝ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።

ኃላፊዋ፤ ወረርሽኙ ከተጀመረ ወዲህ 300 ሚሊዮን ገደማ ዓይነቶችን እንዳጓጓዙና 80 በመቶ የበይነ መረብ ግብይትን እንደተወጡ አሳውቀዋል።

የአውስትራሊያ ፖስታ አገልግሎት ኃላፊ ሆነው ከመሾማቸው በፊት የአውስትራሊያ ቫይታሚን ኩባንያ የሆነው ብላክሞርስ ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል።

እሳቸውን ተክቶ የፓስታ ቤት ኃላፊ የሚሆነው ግለሰብ በቅርቡ ይፋ ይሆናል።