የትግራይ እና የፌደራል መንግሥት ግጭት፡ የአፍሪካ ህብረት ግጭቱ እንዲቆም ጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, AFrican Union website
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማኅማት የፌደራል መንግሥትና የትግራይ ክልል በአስቸኳይ ግጭት እንዲያቆሙ ጠየቁ።
ኮሚሽነሩ ፋኪ ማኅማት በመግለጫቸው የፌደራል መንግሥቱና የትግራይ ክልል ወደ ድርድር እንዲመጡና ሰላማዊ መፍትሄ እንዲፈልጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የአፍሪካ ህብረት ግጭቱን በማስቆምና መፍትሄ በመፈለግ ደረጃ ድጋፉን እንደሚሰጥ አስታውቋል።
ሊቀ መንበሩ ሁለቱም ወገኖች ከግጭት እንዲታቀቡና፣ የሰብዓዊ መብት እንዲያከብሩና የሰላማዊ ዜጎችን ደህንነት እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርበዋል።
የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ባለፈው እሁድ የአፍሪካ ሕብረት በፌደራል እና ትግራይ መንግሥታት ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ ጦርነቱን እንዲያስቆም እና ከርስ በርስ ጦርነት አገሪቷን እንዲታደግ ጠይቀዋል።
የክልሉ ፕሬዝዳንት ለወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር እና የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት በጻፉት ደብዳቤ ሁሉን አካታች የሆነ ውይይት እንዲካሄድ ጠይቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ማክሰኞ እለት በሰጡት መግለጫ "ታደራዊው ዘመቻ የሚቆመው "ህገወጥ" ብለው የጠሩት ቡድን ትጥቅ ፈትቶ በክልሉ ህጋዊ አስተዳደር ተቋቁሞና የፍትህ ተሳዳጆች ወደ ፍትህ እስከሚቀርቡ ድረስ ይቀጥላል ብለዋል።








