ኮሮናቫይረስ፡ የፋይዘር ክትባት በአሜሪካ ጥቅም ላይ እንዲውል ምክር ሃሳብ ቀረበ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ የምግብና መድሃኒት አስተዳደር መሠሪያ ቤትን (ኤፍዲኤ) የሚያማክሩ ባለሙያዎች በፋይዘር/ባዮንቴክ የበለጸገው የኮሮረናቫይረስ ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል ሀሳብ ማቅረባቸው ተገለጸ።
ባለሙያዎቹ ይህን ምክረ ሃሳብ የሰጡት 23 አባላት ያሉት የባለሙያዎች ቡድን ክትባቱ ሊፈጥረው የሚችለው ስጋት ከሚሰጠው ጥቅም አንጻር ምን ሊመስል እንደሚችል ምክክር ካደረጉ በኋላ ነው ተብሏል።
የፋይዘር/ባዮንቴክ ክትባት እስካሁን በዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ፣ ባህሬን እና ሳኡዲ አረቢያ ጥቅም ላይ ለመዋል ፍቃድ አግኝቷል።
በፋይዘር/ባዮንቴክ የተመረተው ክትባት በአሜሪካ ጥቅም ላይ እንዲውል የኤፍዲኤ ይሁንታ ማግኘት ያለበት ሲሆን በሚቀጥሉት ቀናት ይሄው ይሁንታ እንደሚገኝ ይጠበቃል።
አሜሪካ ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ ከ3 ሺ በላይ ሰዎች በኮሮረናቫይረስ ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉን አስታውቃለች።
ይህ ደግሞ በአገሪቱም ሆነ በዓለም እስካሁን በአንድ ቀን ውስጥ ከፍተኛው የሟቾች ቁጥር መሆኑ ተገልጿል።
የአሜሪካ የጤና ሚንስትር አሌክስ ረቡዕ ዕለት ''በሚቀጥሉት ቀናት ክትባቱ በእጃችን ሊገባ ይችላል፤ በሚቀጥለው ሳምንት ደግሞ እጅግ ተጋላጭ የሆኑትን ዜጎች መከተብ ልንጀምር እንችላል'' ብለዋል።
የትራምፕ አስተዳደር 'ራፕ ስፒድ' ብሎ በሚጠራው የክትባት ማከፋፈል ፕሮግራም መሠረት ክትባቱ ፈቃድ ባገኘ በ24 ሰዓታት ውስጥ ማከፋፈል ይጀምራል ተብሏል።
ፋይዘር በያዝነው የፈረንጆቹ ታህሳስ ወር መጨረሻ አካባቢ 6.4 ሚሊየን የክትባት ብልቃጦችን ለማቅረብ እቅድ ይዟል። ሁለት ብልቃጦች በሁለት ሳምንት ልዩነት ለአንድ ሰው ስለሚሰጡ ይህ 6.4 ሚሊዮን ክትባት ለ3.2 ሚሊየን ሕዝብ መከተብ የሚቻለው። አሜሪካ ደግሞ ያላት የሕዝብ ቁጥር 330 ሚሊየን ነው።
የአሜሪካ በሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል እንዳለው በአገሪቱ የሚገኙ 3 ሚሊየን የእድሜ ባለጸጋዎች እና 21 ሚሊየን የሚሆኑ ጤና ላይ የሚሰሩ ሰዎች ቅድሚያ ክትባቱን ያገኛሉ።
በመቀጠል ደግሞ 87 ሚሊየን የሚሆኑ ወሳኝ የስራ ሂደቶች ላይ የተሰማሩ ሰዎች ክትባቱን እንደሚያገኙ የተገለጸ ሲሆን የትኛው የስራ ዘርፍ ቅድሚያ ይሰጠው የሚለውን ግን እያንዳንዱ ግዛት የራሱን ውሳኔ ያስተላልፋል።
በሞደርና እና በብሄራዊ የጤና ኢንስቲትዩት የተሰራው ሌላኛው ክትባትም ቢሆን አሜሪካ ውስጥ ጥቅም ላይ እንዲውል ተጠይቋል። ይህም ክትባት ልክ እንደ ፋይዘር ሁለት ጊዜ ነው የሚወሰደው።












