ሞሮኮ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ለማሻሻል ተስማማች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images/EPA
ሞሮኮ ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመጀመር ከተስማሙ የአረብ አገራት ዝርዝር ውስጥ ተካታለች።
በአሜሪካ አደራዳሪነት የተደረሰውን ስምምነት ፕሬዝደንት ትራምፕ በትዊተር ገጻቸው ይፋ አድርገዋል።
ሞሮኮ ከእስራኤል ጋር ከስምምነት መድረሷን ተከትሎ በዌስተርን ሳሃራ ግዛት ለምታነሳው የይገባኛል ጥያቄ አሜሪካ እውቅና ለመስጠት ተስማምታለች።
በአልጄሪያ የሚደገፉ ፖሊሳሪኦ ግንባር በዌስተርን ሰሃራ የራስ ገዝ አስተዳደር ለመመስረት ከሞሮኮ ጋር ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ አለመግባባት ውስጥ ነበሩ።
ሞሮኮ ከነሐሴ ወር ወዲህ ከእስራሴል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማሻሻል ከስምምነት የደረሰች አራተኛዋ አገር ሆናለች።
በቅርቡ የትራምፕ አስተዳደር ሱዳን፣ ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ እና ባህሬን ከእስራኤል ጋር ሰላም እንዲያወርዱ ማደራደሩ ይታወሳል።
ከዚህ ቀደም ከእስራኤል ጋር የሰላም ስምምነት የፈረሙት ግብጽ እና ጆርዳን ሲደመሩ፤ ከአረብ ሊግ አባል አገራት ከእስራኤል ጋር የሰላም ስምምነት የደረሱት አገራት ቁጥር ወደ ስድስት ከፍ ይላል።
ስምምነቱ ምን ይዟል?
ትራምፕ በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰውን ስምምነት ይፋ አድርገዋል። “ሌላ ታሪካዊ ክስትተ” ብለውታል ፕሬዝደንት ትራምፕ።
ሁለቱ ወዳጅ አራት እስራኤል እና ሞሮኮ ሙሉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመመስረት ተስማምተዋል ብለዋል ተሰናባቹ ፕሬዝደንት።
ዋይት ሃውስ ሞሮኮ ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደምትጀምር፣ ኢኮኖሚያዊ እና ባህላዊ ትብብሮችን ለመጀመር መስማማቷን አስታውቋል።
በራባት እና ቴል አቪዝ የላይዘን ቢሮዎች በፍጥነት ሥራ ለማስጀምር፤ ከዚያም ኤምባሲዎች ለመክፈት ተስማምተዋል ተብሏል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በቴሌቪዥን በተላለፈው ንግግራቸው ስምምነቱን “ታሪካዊ” ያሉት ሲሆን፤ ለሞሮኮ ንጉስ ሞሐመድ ስድስተኛ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ሞሮኮም ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመጀመር መስማማቷን የንጉሱ ቤተ-መንግሥት አረጋግጧል።
ግብጽ፣ ዩኤኢ እና ባህሬን፤ ሁለቱ አገራት የደረሱትን ስምምነት በደስታ ተቀብለነዋል ብለዋል።
የፍልስጤም መሪዎች ግን ስምምነቱን አጥላልተውታል።
ፍልስጤማውያን የአረብ ሊግ አባላት ከእስራኤል ጋር የሰላም ስምምነት ማድረጋቸውን ሲቃወሙ ቆይተዋል።
የፍልስጤም መሪዎች እስራኤል ከአረብ አገራት ጋር ዲፕሊማሲያዊ ግንኙነት እንድትጀምር መፈቀዱ መብታችንን እንድትጋፋ የሚያበረታታ ነው ብለዋል።












