ትግራይ፡ የአውሮፓ ሕብረት እርምጃውን የወሰደው በተሳሳተ ግምገማ ላይ ተመስርቶ ነው- ኢትዮጵያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአውሮፓ ሕብረት ለኢትዮጵያ ከመደበው የበጀት ድጋፍ ውስጥ 90 ሚሊዮን ዮሮ (110 ሚሊዮን ዶላር) እንዲዘገይ ያሳለፈው ውሳኔ በተሳሳተ ግምገማ ላይ የተመሰረተ ነው ሲል የኢትዮጵያ መንግሥት ቅሬታውን ገለጸ።
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሕብረቱ የደረሰበት ውሳኔ "ሁኔታውን በተገቢው ሁኔታ ካለመገንዘብ" የተወሰደ ነው ሲሉ ገልፀውታል።
ሕብረቱ ለቢቢሲ እንዳስታወቀው የያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት ከመገባደዱ በፊት ለኢትዮጵያ ሊሰጥ ይችል ከነበረው 90 ሚሊዮን ዩሮ የበጀት ድጎማ ገንዘብ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲዘገይ ተወስኗል።
ሕብረቱ በቀጣይ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ለኢትዮጵያ ሊያደርግ የነበረው የ90 ሚሊዮን ዮሮ የክፍያ ውሳኔ ወደ ሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ የተደረገው በሰሜን ኢትዮጵያ ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ ነው።
"አሁን ባለው ሁኔታ የአውሮፓ ሕብረት የበጀት ድጋፍ የሚያደርግበት ሁኔታ ላይ አይደለም" ብለዋል የአውሮፓ ሕብረት ቃል አቀባይ ፒሶኔሮ ሄርናንዴዝ ለቢቢሲ በላኩት የኢሜይል መልዕክት።
አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ሙፍቲ በበኩላቸው የአውሮፓ ሕብረት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በተገቢው መንገድ አለመረዳቱን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ሕብረት ጋር ስትራቴጂካዊ የሆነ ግንኙነት የመፍጠር ፍላጎት እንዳላት ያመለከቱት አምባሳደሩ፣ በአገር ውስጥ እየተወሰደ ያለውን "ሕግ ማስከበር እርምጃ ካለመረዳት፣ ይህንንም በማይሆን መንገድ የመተርጎም አዝማሚያ ነው ያለው" ብለዋል።
ይህ ኢትዮጵያ እየወሰደችው ያለው እርምጃ በእያንዳንዱ የአውሮፓ አባል አገራት ዘንድ ሳይሆን፣ በሕብረቱ ደረጃ "የታየ ግርታ" መሆኑን የገለፁት አምባሳደሩ፣ "ግርታውን ለማጥራት ጥረት እናደርጋለን" ብለዋል።
እርምጃው በተሳሳተ ግምገማ ላይ ተመስርቶ የተወሰደ ነው ያሉት አምባሳደሩ ይህም "አሳዛኝ፣ መሆን ያልነበረበት እና ተገቢ ያልሆነ" በማለት ገልፀውታል።
ሕብረቱ ውሳኔውን በተመለከተ የበጀት ድጋፍ የሚያደርገው ቀድሞ ስምምነት የተደረሱባቸው ጉዳዮች መሟላታቸው ሲረጋገጥ እና እንደአስፈላጊነቱ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ከግምት እየገቡ ነው ብሏል።
በዚህም መሠረት የአውሮፓ ሕብረት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን የበጀት ድጎማ ማድረጉን የሚቀጥለው የኢትዮጵያ መንግሥት የሚከተሉትን መስፈርቶች አሟልቶ ሲገኝ እንደሆነ አመልክቷል።
- በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ሰዎች ድጋፍ እንዲያገኙ የሰብዓዊ እርዳታ የሚሰጡ ድርጅቶች እንዲገቡ ፍቃድ ሲሰጥ
- ሰላማዊ ሰዎች ወደ ጎረቤት አገራት መጠጊያ ፍለጋ እንዲጓዙ ሲፈቀድላቸው
- ብሔርን መሠረት ያደረጉ እርምጃዎች እና የጥላቻ ንግግሮች ሲቆሙ
- ተከስተዋል የሚባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር የሚያስችል የአሰራር ዘዴ ሲዘረጋ
- መገናኛ ብዙሃን ወደ ትግራይ እንዲሄዱ ሲፈቀድ እና በትግራይ የግንኙነት መስመሮች ሙሉ በሙሉ ሲከፈቱ የሚሉ መስፈርቶችን ሕብረቱ አስቀምጧል።
ይሁን እንጂ ሕብረቱ በኢትዮጵያ እያከናወናቸው ያሉት ሌሎች የሰብዓዊ ፕሮግራሞች እና ሌሎች ልማታዊ ፕሮግራሞች በዚህ የድጋፍ መዘግየት ውስጥ እንደማይካተቱ ተገልጿል።
ሮይተርስ በአውሮፓ ሕብረት ውሳኔ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ምላሽ ምን እንደሆነ ለማወቅ ባደረገው ሙከራ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ የገንዘብ ሚኒስቴርን እንዲያናግር በመሩት መሰረት ለጥያቄው ምላሽ አለማግኘቱን ጠቅሷል።
የአውሮፓ ሕብረት በዓመት በአማካይ 214 ሚሊዮን ዩሮ የልማት ድጋፍ ለኢትዮጵያ እንደሚሰጥ የሕብረቱ ድረ ገጽ ያመለክታል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው እና ከስድስት ሳምንታት ባላይ ባስቆጠረው ግጭት ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ሰዎች ሲሞቱ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ቤት ንብረታቸውን ጥለው ሸሽተዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግጭቱን በመሸሽ ወደ ሱዳን የተሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ወደ 50 ሺህ እንደሚጠጋ አስታውቋል።
በትግራይም ያለው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነው ሲል ተመድ መግለጫዎችን አውጥቶ የነበር ሲሆን፤ በትግራይ የሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን እና የመድኃኒት እና ምግብ እጥረት እንደተከሰተም አስታውቆ ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግሥት የትግራይን መዲና መቀለን ከህወሓት ኃይሎች መቆጣጠሩን ይፋ ካደረገ በኋላ ክልሉን መልሶ የመገንባታ እና የሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው እርዳታ የማቅረብ ሥራ እንደሚከናወን አስታውቆ ነበር።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባደረጉት ንግግርም ኢትዮጵያ ስደተኞችን መልሶ ማቋቋም ላይ ያላትን ልምድ በማውሳት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ስደተኞችን መልሶ ማቋቋሙ ለአስተዳደራቸው ከባድ የቤት ሥራ እንደማይሆን ተናግረዋል።
ከቀናት በፊትም የሰብዓዊ እርዳታ ቁሳቁሶችን የጫኑ ከባድ ተሽከርካሪዎችም ወደ ትግራይ ከተሞች ሲገቡ ነበር።
ከዚህ በተጨማሪም ባለፉት ጥቂት ቀናት መቀለን ጨምሮ በትግራይ አንዳንድ ከተሞች የኤሌክትሪክ ኃይል እና የቴሌኮም አግልግሎቶች ዳግም ወደ ሥራ እየገቡ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የአራት ብሔራዊ ፓርቲዎች ጥምረት የነበረውን ኢህአዴግ በማክሰም ብልጽግና ፓርቲን እንዲመሰረት ማድረጋቸውን ተከትሎ ማዕከላዊው መንግሥት ከህወሓት ጋር የነበረው ግንኙነት መበላሸቱ ይታወሳል።
በተለይ ባለፈው ዓመት መካሄድ የነበረበትና በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ የተላለፈው ምርጫ ነገሮችን በከፍተኛ ደረጃ እንዲካረሩ አድርጓል።
በበሽታው ምክንያት የፌደራልና የክልል ምክር ቤቶች የስልጣን ዘመን ምርጫው አስኪደረግ ድረስ ለአንድ ዓመት እንዲራዘም ሲወሰን ህወሓት ግን "ሕገወጥ እርምጃ ነው" በማለት ተቃውሞውን አሰምቶ በትግራይ ክልል የተናጠል ምርጫ አካሂዷል።
ይህ ህወሓት ያካሄደው ክልላዊ ምርጫ፤ ከምርጫ ቦርድ፣ ከፌደራል መንግሥቱና ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ተቀባይነትን አላገኝም ነበር።
መጀመሪያም ምርጫው ተቀባይነት የለውም በማለት ሲያስጠነቅቅ የነበረው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፌደራል መንግሥቱ ከክልሉ መስተዳደር ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳያደርግ በማዘዘዝ በጀት የማቀብ እርምጃ ወሰደ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ነበር ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የህወሓት ኃይሎች በትግራይ ክልል የሚገኘውን ከአገሪቱ ሠራዊት ትልቁ ክፍል የሚባለውን የሠሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ማድረሳቸው የተነገረው።
ይህንንም ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በህወሓት ኃይሎች ላይ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ካዘዙ በኋላ በምድርና በአየር ለሦስት ሳምንታት ያህል የዘለቀ ዘመቻ ተካሂዶ የክልሉ ዋና ከተማ በአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት እጅ ስትገባ መንግሥት ሕግ የማስከበር ያለው ወታደራዊ ዘመቻ ማብቃቱን ማሳወቁ ይታወሳል።
















