ኢትዮጵያ የወሰደችው ቆራጥ እርምጃ ነው - ሙሳ ፋኪ መሐማት

ሙሳ ፋኪ ማኅማት

የፎቶው ባለመብት, AFrican Union website

የኢትዮጵያ መንግሥት የአገሪቱን አንድነትና መረጋጋት ለማረጋገጥ የወሰደው እርምጃ ቆራጥነት የተሞላበት መሆኑን የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ተናገሩ።

ሙሳ ፋኪ ማሐማት ይህንን የተናገሩት ትናንት እሁድ ጂቡቲ ውስጥ በተካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) 38ኛ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ነው።

የሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ጨምረውም የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት የወሰደው እርምጃ "የአገሪቱን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ለማስከበር" መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም ሁሉም አገራት የሚጠበቅባቸው ሕጋዊ ኃላፊነት መሆኑንም አመልክተዋል።

ሙሳ ፋኪ እንዳሉት በዚህ በትግራይ ክልል ውስጥ የተከሰተውን ቀውስ ተከትሎ ከፍተኛ መጠን ያለው መፈናቀል መከሰቱን ገልጸው፤ በዚህ ረገድ ኢጋድ ለስደተኞችና ለተፈናቀሉ ሰዎች የተለየ ትኩረት በመስጠት ኢትዮጵያ ከምታደርገው የሰብአዊ ድጋፍ ጥረት ከጎኗ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

ኮሚሽነሩ ፋኪ ማሐማት ከዚህ በፊት፣ የፌደራል መንግሥቱና የትግራይ ክልል ወደ ድርድር እንዲመጡና ሰላማዊ መፍትሄ እንዲፈልጉ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

ለአንድ ቀን በተካሄደው በዚህ ጉባኤ ላይ የተሳተፉት የኢጋድ አባል አገራት ከአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር በተጨማሪ ለኢትዮጵያ መንግሥት ድጋፋቸውን መግለጻቸው ተነግሯል።

ይህንንም ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ የአገራቱ መሪዎች "የሕግ ማስከበር እርምጃዎቻችንን ሕጋዊነት በመረዳታቸውና እውቅና በመስጠታቸው እንዲሁም ኢትዮጵያን ለመደገፍ ቁርጠኝነታቸውን በመግለጻቸው" ምስጋና አቅርበዋል።

በጥቅምት ወር የመጨረሻ ሳምንት ላይ በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል የተቀሰቀሰው ወታደራዊ ግጭት ከኢትዮጵያ አልፎ በአካባቢው አገራት ላይ ተጽእኖ እንደሚኖረው ሲነገር የነበረ ሲሆን፤ የኢጋድ አባላት ጉዳዩን አንስተው መወያየታቸው ተነግሯል።

ለሳምንታት የዘለቀው ወታደራዊ ግጭት የኢትዮጵያ ፌደራል ሠራዊት የትግራይ ክልል ዋና ከተማን ከተቆጣጠረ በኋላ መንግሥት "ሕግ የማስከበር ዘመቻ" ያለው መጠናቀቁን መግለጹ ይታወሳል።

በወታደራዊ ግጭቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት ሳይጠፋ እንዳልቀረ የተገመተ ሲሆን፤ በአገር ውስጥ እንደተፈናቀሉ ከሚገመቱ ሰዎች ባሻገር ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች ግጭቱን ሸሽተው ወደ ሱዳን መሰደዳቸውን የረድኤት ድርጅቶች ይናገራሉ።

የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) በዚህ ባካሄደው አስቸኳይ ልዩ ስብሰባው ላይ በአባል አገራቱ ውስጥና በአገራት መካከል ባሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በመነጋገር አፋጣኝ እርምጃ በሚያስፈልጋቸው ላይ ውሳኔዎችን ሰጥቷል።

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባ ላይ አግኝተዋቸው ከነበሩት ከሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ፣ ከኬንያው ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ ከሶማሊያው ፕሬዝደንት ሞሐመድ ፋርማጆ፣ ከደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝደንት እንዲሁም ጅቡቲው ፕሬዝደንት ኢስማኤል ኦማር ጉሌህ ጋር ተወያይተዋል።

መሪዎቹ በአባል አገራት ውስጥ እንዲሁም በአንዳንድ አገራት መካከል ስላሉ ጉዳዮች አንስተው መወያየታቸው ተገልጿል።

መቀመጫውን በጂቡቲ ያደረገው የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ኤርትራን፣ ሱዳንን፣ ኢትዮጵያን፣ ጂቡቲን፣ ደቡብ ሱዳንን፣ ኬንያን፣ ሶማሊያንና ኡጋንዳን በአባልነት የያዘ ቀጠናዊ ተቋም ነው።