ትግራይ ፡ ግጭት ሸሽተው ለስደት የተዳረጉ የሁለት ሐኪሞች ምሥክርነት

የፎቶው ባለመብት, AFP
ሁለት ኢትዮጵያዊያን ሐኪሞች በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ያዩትን አሰቃቂ ሁኔታ ለቢቢሲ አጋርተዋል።
ዶ/ር ቴዎድሮስ ተፈራ ሑመራን ጥሎ የሸሸ ሐኪም ነው። በኋላ ደግሞ አደባይ የምትባለዋን ከተማ ጥሎ ወደ ሱዳን ሄደ። ለቢቢሲ እንደተናገረው ሁለቱም ቦታዎች ለሕይወቱ አደገኛ ነበሩ።
ሁለተኛው ሐኪም ስሙን ለመናገር አይሻም። ለአንዲት ሕይወቷ አደገኛ ሁኔታ ላይ ለነበረች ሴት በሞተር ሳይክል ላይ ሆኖ ሕክምና እንዳደረገላት ይናገራል፤ ነገር ግን አሁን በህይወት ትኑር አያውቅም።
ሁለቱም ሐኪሞች ዘግናኝ የሚባሉ የንጹሐንን ሞት እንደተመለከቱ ለቢቢሲ ተርከዋል።

መነሻ
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እግረኛና አየር ኃይሉ በህወሓት ላይ ዘመቻ እንዲያካሂድ ትዕዛዝ የሰጡት የክልሉ ልዩ ኃይል በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ነበር።
ሠራዊቱ ኅዳር 19/2013 ዓ.ም መቀለን ሲቆጣጠር ዐቢይ አህመድ የኢትዮጵያ ሠራዊት በንጹሐን ላይ አንድም ጉዳት አላደረሰም ብለው ነበር።
በተመሳሳይ፣ ምንም እንኳ ህወሓት ወደ ኤርትራ ሚሳይሎችን የተኮሰ ቢሆንም የኤርትራ መንግሥት በዚህ ጦርነት እጁን እንዳላስገባ አስተባብሏል።
ገለልተኛ የሆኑ መረጃዎችን ለማግኘት በአካባቢው የግንኙነት መስመሮች ሙሉ በሙሉ ባለመጀመራቸው አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል።
30ሺህ ነዋሪዎች ያሏት የሑመራ ከተማ በዚህ ጦርነት ጉዳት ከደረሰባቸወ ቀዳሚ ከተሞች አንዷ ናት። ግጭቱ የተጀመረውም ጥቅምት 27/2013 ዓ.ም ነበር።
የሁለቱን ሐኪሞች ምሥክርነት እንደሚከተለው ይቀርባል።
ማሳሰቢያ፡ ይህ ጽሑፍ የጦርነት ጉዳቶችን የሚገልጹና የሚያውኩ አንቀጾችን መያዙን ከወዲሁ እናሳስባለን።
የዶ/ር ቴዎድሮስ ምሥክርነት
የከባድ ጦር መሣሪያ ድብደባዎች ነበሩ። ድብደባዎቹ በሑመራ ከተማ ሁሉንም ቦታዎች ኢላማ ያደረጉ ነበሩ። የገበያ ሥፍራዎችን፣ የቤተ ክርስቲያን አካባቢን፣ የመስጊዶች አካባቢን፣ ብሎም የሆስፒታል ግቢ ላይ ድብደባ ነበር።
በመጀመሪያው ቀን ወደ 15 ሬሳ መቀበላችንን አስታውሳለሁ። እንዲሁም 75 ቁስለኞችንም ተቀብለን ነበር። ከሰዓት በኋላም ድብደባው አላቋረጠም ነበር።
ወደ ሑመራ ከተማ ድብደባው ይመጣ የነበረው ከምሥራቅ አቅጣጫ ነበር። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በምሥራቅ አቅጣጫ ነበረ።
ከሰሜን አቅጣጫ ደግሞ ከሑመራ በቅርብ ርቀት ላይ ከሚገኘው ከኤርትራ በኩልም ይተኮስ ነበረ። ድብደባው ከኤርትራ በኩልም ይመጣ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም።
በሁለተኛው ቀን፣ ድብዳው በጠዋት ነበር የተጀመረው።
ልክ 5፡00 ሰዓት አካባቢ ግን ረገብ ማለት ጀመረ። ያን ቀን 8 አስከሬኖች ተቀብለናል። በርካታ የቆሰሉ ሰዎችንም ተቀብለናል። ከዚህ በኋላ ግን ነገሩ ለእኛም ሆነ ለበሽተኞቻችን ደኅንነት አስጊ እንደሆነ ተረዳን።
ስለዚህ ከዚያ ቦታ ለመልቀቅ ወሰንን።
የቆሰሉ በሽተኞቻችንን ተሳቢ መኪና ላይ ጫንናቸው። ከዚያም ወደ አደባይ ከተማ ሄድን።
አደባይ ከሑመራ 30 ኪሎ ሜትር ብትርቅ ነው። እዚያ ድብደባ አልነበረም። ነገር ግን ጦርነቱ ቀጥሎ ነበር።
በአደባይ ክሊኒክ ውስጥ በሽተኞቻችንን ማከሙን ቀጠልን። በርካታ ንጽሐን ከሑመራ እየመጡ ነበር።
በመጀሪያው ቀን የምናክማቸው ሰዎች ከድብደባው ጉዳት የደረሰባቸወ ነበሩ።
የመንግሥት ወታደሮች ሑመራ ከተማ ከገቡ ወዲህ ግን ወደእኛ እየመጡ የነበሩ ሰዎች የድብደባ ምልክት እና በስለት ጉዳት የደረሰባቸው ነበሩ።
እንደነገሩን ከሆነ ደረት ላይ ባጅ ያለበት ዩኒፎርም የለበሱ የአማራ ልዩ ኃይል አባላት እና ፋኖ የሚባሉ ዩኒፎርም የማይለብሱ የሚሊሻ አባላት ሑመራ ደርሰው ነበር።
በምዕራብ ትግራይ የተለያዩ ቦታዎች የሚከተሉት ሁኔታዎች ተከስተዋል፡-
- መጀመሪያ የጦር መሣሪያ ድብደባ ነበር
- ከዚያ የመንግሥት ወታደሮች ገቡ
- ከዚያ ደግሞ የአማራ ልዩ ኃይልና ፋኖዎች ተከተሉ
አደባይ ሆነን ቁስለኞችን የማከሙን ነገር ለሁለት ቀናት ቀጠልንበት። ከዚያም ውጊያው በጣም እየተባባሰ መጣ። ወደ ክሊኒኩም እየቀረበ ነበር።
አሁን ደግሞ በሽተኞቻችንን ጦርነቱ ብዙም ወዳዳልተፋፋበት ወደ ሌላ የትግራይ ክፍል በጭነት መኪና መውሰድ አለብን አልን። ወደዚያም በእግር ተጓዝን።

የፎቶው ባለመብት, AFP
እዚያው ጫካ ውስጥ ለሁለት ቀናት ተደበቅን። በሦስተኛው ቀን ሁኔታው ለደኅንነታችን አስፈሪ እየሆነ መጣ። ምክንያቱም ግድያው ትርምሱ በአደባይ ከተማ እየተፋፋመ መሄዱ ነበር። ከአደባይ አቅጣጫ ድብልቅልቅ ያለ የተኩስ ድምጽ ይሰማን ነበር።
ከዚህ በኋላ ነበር በእግር ወደ ሱዳን የድንበር ከተማ ሐምዲያት የተሻገርነው። ሐምዲያት እኛ ከነበርነበት 50 ኪሎ ሜትር ቢርቅ ነው።
ሚሊሻዎች ግን በጫካው ውስጥ እየተሸሎኮለኩ በተከዜ በኩል ይከተሉን ነበር።
አሁን ያለሁት በስደተኞች መጠለያ ውስጥ ነው። አሁንም እዚህ በሽተኞችን እየረዳሁ እገኛለሁ።
ከብዙ የትግራይ አካባቢዎች በሽተኞች መምጣታቸውን አላቆመም።
ከድንበር 300 ኪሎ ሜትር ከራቁ አካባቢዎች ጭምር የሚመጡ በሽተኞች አሉ። (ወደ ካምፑ የመጡ በሽተኞች) የሰዎችን ሬሳን በየመንገዱ እየተመለከቱ እንደመጡ ይነግሩናል።
የኤትርራ ሠራዊት ቤቶችን እንዳቃጠለ፣ ሰብል እንዳወደመና ብዙ ሰብአዊ ጥፋቶችን እንዳደረሰ የሚነግሩኝ በሽተኞችም አሉ።
ይህ ሁሉ የሆነው በጨለማ ነው፤ ኢንተርኔት በሌለበት፣ ኤሌክትሪክ በሌለበት ባንክ በተዘገባት ሁኔታ። ትግራይ ውስጥ ምን እየሆነ እንደሆነ በትክክል የሚያውቅ ማንም የለም።
የተናገርኩት ካየሁትና ከሰማሁት ነው። እውነት ነው የምመሰክረው። በቀጣይ ገለልተኛ ቡድን ተልኮ ሁሉንም ነገር ያጣራል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
ስሙን መግለጽ የማይሻው ሐኪም ምሥክርነት:
ሑመራ ላይ የመሣሪያ ድብደባው ከመጀመሩ ሁለት ቀን ቀደም ብሎ ከፌዴራልና ከክልል ኃይሎች የተጎዱ ወታደሮችና ነዋሪዎችን እየተቀበልን እናክም ነበር።
ጉዳቶቹ በአብዛኛው ከተኩስና ከከባድ መሣሪያ ጋር የተያያዙ ነበሩ። ነገር ግን ቁጥራቸው ብዙም አልነበረም።
ይህ ሁኔታ መቆየት የቻለው ግን የኤርትራና የኢትዮጵያ ሠራዊት ጥቃት እስኪከፍት ብቻ ነበር። ሆስፒታላችን ፊት ለፊት በነበረ ቦታ ራሱ ፍንዳታ ነበር።
ከዚህ በኋላ የሚመጡት በሽተኞቻችን ንጹሐን ነበሩ።
በዚያ ቀን ብቻ እኔ በነበርኩበት የሆስፒታሉ ክፍል 200 ሰዎችን ተቀብለናል። ወደ 50 የሚሆኑት ደግሞ ሆስፒታል ሲደርሱ ሙት ነበሩ።
ወጣቶች የቆሰሉ ሰዎችን በባጃጅ እየጨኑ ወደኛ ያመጧቸው ነበር። የሆስፒታል አልጋ እጥረት ነበር። አንዳንዶቹ በሽተኞችን እናክም የነበረው በሆስፒታል ወለል ላይ ሆነው ነበር። ሌሎችን ደግሞ ደጅ ላይ ጭምር።
ግጭቱ ከመጀመሩ በፊት በተለያዩ ህመሞች ሆስፒታል የነበሩ 200 በሽተኞች ነበሩን። ግጭቱ ሲጀመር ግን አብዛኞቹ አልጋቸውን ለቆሰሉ በሽተኞች መልቀቅ ነበረባቸው፤ የራሳቸውን ህምም ትተው ቁስለኞቹን ይንከባከቧቸውም ነበር።
ነገር ግን እንደ ሐኪም ብዙ ሕይወት ማዳን አልተቻለምን። ምክንያቱም በደም ባንክ ውስጥ በቂ የደም ክምቸት አልነበረንም። ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥርም ከአቅም በላይ ነበር።
ስለዚህ ማድረግ የቻልነው የተወሰነ የመጀመርያ ደረጃ እርዳታ መስጠት ብቻ ነበር። ብዙ በሽተኞች አይናችን እያየ (መዳን እየቻሉ) እጃችን ላይ ይሞቱ ነበር። ያን ቀን ብቻ እስከ ምሽት 4፡00 ሰዓት ስንሠራ አመሸን።
የነበርንበት ቦታ ለደኅንነት አስጊ እየሆነ ስለመጣ አንዳንድ የሆስፒታል ባልደረቦቻችን ወደ አደባይ መሄድ ጀመሩ። ሌሎች ግን እዚያው ለመቆት ወሰኑ።

የፎቶው ባለመብት, AFP
እኔም ወደ አደባይ ሄድኩኝ። የተወሰኑ በሽተኞችን ከእኛ ጋር ይዘን ለመሄድ መኪና አዘጋጀን። ስድስት በሽተኞች ከኢትዮጵያ ሠራዊት አብረውን ነበሩ።
አደባይ እንደደረስን በክሊኒኩ ውስጥ በጠዋት ሥራ ጀመርን። 10 የሚሆኑ በሽተኞች ከሑመራ የመጡ ነበሩ።
ሆዷ ላይ የቆሰለች አንዲት እናት ወንድ ልጇ ይዟት መጥቶ ነበር። አንጀቷ ከሆዷ በኩል ተንጠልጥሎ ደም እየፈሰሳትም ነበር። ልጇ ከሑመራ ድረስ በሞተር ሳይክል ተሸክሟት መምጣቱ ጥንካሬው ይገርማል። አሁን በሕይወት ትኑር አትኑር አላውቅም። ሆኖም የመጀመርያ እርዳታ አድርጌላት ነበር።
በዚህ ሁኔታ ለሦስት ቀናት ያህል በሽተኞቹን ለመርዳት ሞከርን። ከዚያ በኋላ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት መጥተው እያከምናቸው የነበሩ ወታደሮችን ይዘዋቸው ሄዱ።
በአደባይ በንጽሐን ላይ ሲተኮስ ነበር። እኛም ከአደባይ ቅርብ በነበረበ ቦታ ሄደን መደበቅ ነበረብን። ማታ ማታ ግን ተመልሰን ወደ ክሊኒኩ እየሄድን በሽተኞችን እናክም ነበር።
በአምስተኛው ቀን፣ ከዚህ በኋላ ለሕይወታችን አስጊ ነው ብለን ወደ ሱዳን ሄድን።
ከሑመራ ይዘናቸው የመጣናቸውን አንቲባዮቲክና ሌሎች መድኃኒቶችን በክሊኒኳ ውስጥ ለነበሩ ባልደቦች ትተንላቸው ወጣን።
'እጁ የተቆረጠው ወጣት'
ብዙ ሰዎች ለአራት ቀናት ያህል ሱዳን ለመግባት ተጉዘዋል። እኔ ግን ዕድለኛ ነኝ። ሞተር ያለው ልጅ አውቅ ስለነበር እኔና ባለቤቴን በሞተር ድንበር ድረስ ወሰደን። በአንድ ቀን ከግማሽ ሐምዳይት ገባን።
ስንደርስ አንድ ወጣት አየሁ። ጭንቅላቱ ላይ ከመቁሰሉም በላይ እጁ ተቆርጧል። ከማይካድራ እንደመጣ ነገረኝ። ለአምስት ቀናት መድኃኒት ሰጠሁት።
እዚህ በጣም ብዙ ሰዎችን አገኘሁ። ሁሉም የትግራይ ተወላጆች ናቸው። በማይካድራ በነበረው ጥቃት ወቅት ጉዳት የደረሰባቸው ቢሆንም በእጄ ላይ የማክምበት መሳሪያ ስላልነበረኝ የሕክምና እርዳታ ልሰጣቸው አልቻልኩም።
[መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በማይካድራ ከ600 በላይ የአማራ ተወላጆች በህወሓት ሚሊሻዎች መገደላቸውን መግለጹ ይታወቃል።]
አሁን ወደ ኡም ራኮባ የስደተኞች ካምፕ ገብቻለሁ። ከሀምዳይት የ8 ሰዓት የመኪና ጉዞ ይርቃል። እዚህ በብዛት የሱዳን ህመምተኞች ናቸው የሚመጡት። ብዙዎቹ የደረት ኢንፌክሽንና ተቅማጥ ነው ያለባቸው።
እንደምንረዳቸው እንነግራቸዋለን። ሆኖም አገር ቤትን ሳስብ ያመኛል። ኦክሲጅን አጥተው የሚሞቱትን ወገኖቼን ሳስብ፣ በጥይት ተመተው የቆሰሉ ዜጎችን ሳስብ ያመኛል። እንዲሞቱ የተፈረደባቸው ናቸው።
ደግሞም ጥፋተኝነት ይሰማኛል። እነሱን ሳስብ ድብታ ውስጥ እገባለሁ፤ የአእምሮ ሰላሜን አጣለሁ።













