በአሜሪካ የ'ወሊድ ቱሪዝም' በማጧጧፍ የተከሰሰችው ቻይናዊት

ቻይናውያን ሴቶች ልጆቻቸውን አሜሪካ እንዲወልዱ በማመቻቸት የተከሰሰችው ቻይናዊት ጥፋተኛ መሆኗን አምናለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቱጃር ቻይናውያን ልጆቻቸውን አሜሪካ እንዲወልዱ በማመቻቸት የተከሰሰችው ቻይናዊት ጥፋተኛ መሆኗን አመነች።

የሚወለዱት ልጆች የአሜሪካ ዜግነት እንዲያገኙ፤ እናቶቻቸው ወደ አሜሪካ እንዲጓዙ ያመቻቸችው ቻይናዊት ዶንግዩአን ሊ፤ ክስ የተመሰረተባት አሜሪካ ውስጥ ነበር።

'የወሊድ ቱሪዝም' የሚል ስያሜ ባለው ሂደት፤ አንዲት ሴት ወደ አሜሪካ ሄዳ ለመውለድ ገንዘብ ትከፍላለች። ቻይናዊቷ ዶንግዩአን ያቋቋመችው ድርጅት በኃብት የናጠጡ ቻይናውያን ልጆቻቸው የአሜሪካ ዜግነት እንዲያገኙ ያመቻች ነበር።

ዶንግዩአን፤ ሴቶቹ እርጉዝ መሆናቸው ሳይታወቅ የአሜሪካን ኢሚግሬሽን እንዴት ማለፍ እንደሚችሉ ስልጠና ትሰጥ ነበር። ለአገልግሎቷ በጠቅላላው ከሦስት ሚሊየን ዶላር በላይ ሰብስባለች ተብሏል።

ጥቅምት ላይ በዶንግዩአን ጉዳይ ብይን የሚሰጥ ሲሆን፤ የ15 ዓመት እሥር መከናነቧ እንደማይቀር ተገምቷል።

የ 'ወሊድ ቱሪዝም' ለምን?

እንደ ጎርጎሮሳያውኑ ከ2013 እስከ 2015 ድረስ፤ ቻይናውያን እርጉዝ መሆናቸው ሳይታወቅ የአሜሪካን ኢሚግሬሽን ማለፍ የሚችሉበትን መንገድ ለማሰልጠን ከ40,000 እስከ 80,000 ዶላር ታስከፍል እንደነበረ ዶንግዩአን አምናለች።

'ዩ ዊን ዩኤስኤ ቫኬሽን ሰርቪስ' የተባለው ድርጅቷ የቻይና ባለሥልጣኖችን ጨምሮ ለብዙዎች አገልግሎቱን ሰጥቷል።

የድርጅቱ ድረ ገጽ ላይ የሚገኘው ማስታወቂያ ወደ 500 የሚደርሱ ደንበኞቹ፤ "አሜሪካዊነት ከሁሉም አገሮች በበለጠ የሚያስደስት ዜግነት ነው" ማለታቸውን ይገልጻል።

የዶንግዩአን፤ ደንበኞቿ መጀመሪያ ከቻይና ወደ ሀዋይ ከበረሩ በኋላ ወደ ሎስ አንጀለስ እንዲጓዙ ትመክር ነበር። የአሜሪካ ኢሚግሬሽንን በቀላሉ ለማለፍ መዳረሻን ሀዋይ ማድረግ የተሻለው አማራጭ ሲሆን፤ ደንበኞቿ ከሀዋይ ወደ ሎስ አንጀለስ ከበረሩ በኋላ አፓርትመንት ውስጥ ያርፋሉ።

ዶንግዩአን፤ ደንበኞቿ ለቻይና ኢሚግሬሽን ሠራተኞች፤ አሜሪካ ውስጥ ለሁለት ሳምንት ብቻ እንደሚቆዩ መንገር እንዳለባቸው ታሰለጥናቸው እንደነበርም አምናለች።

ቻይናውያኑ ሴቶች ቢያንስ ለሦስት ወር አሜሪካ ውስጥ ይቆያሉ።

ቻይናዊቷ ቪዛ በማጭበርበር የቀረበባትን ውንጀላ ከተቀበለች በኋላ፤ ወደ 850,000 ዶላር፣ 500,000 ዶላር የሚያወጣ ቤቷን እንዲሁም መርሴደስ ቤንዝ መኪኖቿን ለማስረከብ ተስማምታለች።

የአሜሪካ ሕግ፤ አገሪቱን መጎብኘትና እዛው ሳሉ ልጅ መውለድን አይከለክልም። ሆኖም በሀሰተኛ መረጃ ቪዛ ማግኘት በሕግ ያስቀጣል።

ዶንግዩአን፤ ቻይናውያን ሴቶች አሜሪካ ውስጥ ልጅ ቢወልዱ፤ ቤተሰቦቻቸው ለስደተኞች በወጣ ድንጋጌ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ በመግለጽ ድርጅቷን ታስተዋውቅ ነበር።

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሌሎች አገራት ዜጋ ከሆኑ ቤተሰቦች አሜሪካ ውስጥ ለሚወለዱ ልጆች የአሜሪካ ዜግንት የሚሰጥበትን አሠራር የማገድ እቅድ እንዳላቸው መናገራቸው ይታወሳል።