ኢትዮጵያ፡ በጂንስ የተሞሸሩት ጥንዶች

ኦልያድ እና ቢፍቱ

የፎቶው ባለመብት, ኦልያድ እና ቢፍቱ

የምስሉ መግለጫ, ኦልያድ እና ቢፍቱ ቃለ መሃላ ሲፈጽሙ

ኦልያድ ኤልያስ እና ቢፍቱ ኦላና ባሳለፍነው እሁድ ነበር የሠርግ ስነ ስርአታቸውን የፈጸሙት። ታዲያ በሰርጋቸው ዕለት ሙሽራዋ በቬሎ ቀሚስ አጊጣ ሙሽራውም ሙሉ ልብሱን ሽክ ብሎ አልነበረም የተሞሸሩት።

ጥቅስ የተጻፈበት ተመሳሳይ ቲሸርትና የየራሳቸውን ጅንስ ሱሪ ነበር ሁለቱም ሙሽሮች የለበሱት።

የተጠራ ዘመድ አዝማድም የለም፤ ጥቂት ጓደኞች ብቻ አጀብ አድርገዋቸዋል።

ኦልያድና ቢፍቱ ምን አነሳስቷቸው ይሆን ?

ኦልያድ እንደሚለው ከባለቤቱ ቢፍቱ ጋር ከድሮም ጀምሮ በዚሁ ጉዳይ ላይ ሲወያዩ ከባድ የሰርግ ድግስ አስፈላጊ አለመሆኑን ተስማምተዋል። ዋናው ምክንያታቸው ደግሞ ድል ያለ ሰርግ ለመደገስ ሲባል የሚወጣው ወጪ ለማስቀረትና ቤተሰብና ዘመድ አዝማድን ከድካም ለማዳን እንደሆነ ይናገራል።

አክሎም ''ምንም እንኳን ዋና ሚዜ ሆኜ ባላውቅም አንድ ሁለቴ ሰርግ ሄጄ አውቃለሁ። ሰርጎች ላይ በማየው ነገርም ብዙም ደስተኛ አልነበርኩም። ሰዎች ተቸግረው ሲደግሱ ሳይ ለምን ይህን ያክል እላለሁ'' ይላል።

የኦሊያድ እናት የሆኑት ወ/ሮ ዝናዬ ወዳጆ ደግሞ ልጃቸው ላገባ ነው ማለቱ ሳይሆን ያሳሰባቸው በዚህ ዓመት ትምህርት መጨረሱ ነው። እንደ እናት ጥቂት ጊዜ አረፍ ቢል ሳይሉ አልቀረም።

ልጃቸው ግን ሊያገባ ወሰነ፤ ሰኔ ዘጠኝ 2011ዓ.ም ደግሞ ጋብቻው የሚፈፀምበት ቀን ሆኖ ተቆርጧል።

ኦልያድ ሰኔ ዘጠኝ ማለዳ ከቤቱ ሲወጣ የሰርጉ ዕለት እንደሆነ ቢያውቅም ምንም የተለየ ነገር አላደረገም። ልክ እንደ ሌላ ጊዜው ወደ ቤተክርስቲያን በመሄድ የዕለቱን ትምህርት ተከታትሏል። ፕሮግራሙ ሲያልቅም ለምሳ ከወጣ በኋላ በቤተክርስቲያኒቱ የሚደረገውና ከ8 ሰአት ጀምሮ 10 ሰዓት የሚያልቀውን የወጣቶች ዝግጅት ለመከታተል ተመልሶ ሄደ።

የወጣቶች ትምህርት እየተከታተለ ሳለም እጮኛው ቢፍቱ በቤተክርስቲያኑ ደረሰች። የቤተክርስቲያኑ አባቶችም ስለጉዳዩ ቀድመው ያውቁ ስለነበር በፕሮግራሙ መሃል አንደኛው የሃይማኖት አባት ጥንዶቹ ቃል ኪዳን እንዲፈጽሙ ካደረጉ በኋላ ወደ ዕለቱ ትምህርት ተመለሱ።

''በወቅቱ እኔ እና ባለቤቴ የለበስነው ቲሸርት ተመሳሳይ ነበር። ቲሸርቱ ጥቅስ የተጻፈበት ሲሆን ሌላ ለየት ያለ ምንም አይነት አለባበስ አልነበረም። እኔም ጂንስ ሱሪ ነበር ያደረግኩት።''

''እኔና ባለቤቴ ስለሰርጉ ስነስርአት ቀድመን ስለተስማማን ምንም አለመግባባት አልተፈጠረም። እንደውም ከቤተሰብና ጓደኞች ትንሽ ጫና ነበር። ሁሉም ሰው በቀላሉ ሊቀበለን ፈቃደኛ አልነበረም'' በማለት ኦልያድ ስለሁኔታው ያስረዳል።

ወ/ሮ ዝናዬም የሀገርን ወግና ባህል በማሰብ የልጃቸው ሰርግ እንዲህ በጅንስ ብቻ መሆኑ፣ ወገን እንደሌለው በሰው አለመከበባቸውን መቀበል እንደከበዳቸው አልሸሸጉም። በኋላ ግን የልጆቹን ፍቅር በማየት ይሁንታቸውን ሰጡ።

"ሠርጉ በእንዲህ አይነት ሁኔታ መከናወኑ፣ ዘመድ አዝማድ ባለመጠራቱ የተሰማኝ ቅሬታ የለም" ይላሉ።

ሙሽሪት ቢፍቱ ኦላና በበኩሏ የእኛን ሰርግ ከተመለከቱ በኋላ እንደ ትምህርት ሊወስዱት የሚችሉ ይመስለኛል፤ እንደውም ድል ያሉ የሰርግ ድግሶች እየቀሩ የሚሄዱ ይመስለኛል ትላለች።

''ልክ ሰርግ ሲባል ወደ ጭንቅላታችን የሚመጣው ቬሎ ቀሚስና የወንዶቹ ሙሉ ልብስ መቅረት አለበት ብዬ አስባለሁ። የጋብቻው ዋና አካል ተደርጎ ባይታሰብ ጥሩ ነው። ለትዳር ምንም የሚጨምረው ነገር የለም።'' ስትል ለምን በሰርጋቸው ዕለት ቲሸርትና ሱሪ እንደለበሱ ታስረዳለች።

ጓደኞችሽ ምን አሉሽ በሚል ለቀረበላት ጥያቄ ቢፍቱ ስትመልስ '' ከበፊትም ጀምሮ እነግራቸው ስለነበር አልተገረሙም። ግርግር የበዛበት ነገር እንደማልወድ ያውቁ ነበር።'' ብላለች።

ኦልያድ እና ቢፍቱ

የፎቶው ባለመብት, ኦልያድ እና ቢፍቱ

የምስሉ መግለጫ, ኦልያድ እና ቢፍቱ በሰርጋቸው ዕለት

ወዳጆቿ በሱሪና ቲሸርት የቨርግን እለት ማሳለፍ የሚለውን ሃሳብ ሲሰሙ አብዛኛዎቹ ደስተኛ እንዳልነበሩና ትንሽ እንደከበዳቸው አልሸሸገችም። ጓደኞቿ የባህል ልብስ ወይም ሌላ ለየት ያለ ነገር ጠብቀው እንደነበረም ታስታውሳለች።

'' በቬሎ ደምቆ ከመሞሸሩ ይልቅ ከቤተክርስቲያን አባቶች ምርቃት አግኝቶ ሰርጌን ማሳለፍ ለእኔ ትልቅ ቦታ አለው። ጓደኞቼም ሰርጌን ከተመለከቱ በኋላ በጣም ደስ እንዳላቸውና ብዙ ትምህርት እንደወሰዱበት ነግረውኛል'' ብላለች።

የሰርጋቸው ለየት የማለት ጉዳይ እንደዚህ የብዙ ሰዎችን ቀልብ ሊስብ እንደሚችል አለመገመታቸውን የምትናገረው ቢፍቱ ለየት ብሎ ለመታየት ብለው ያደረጉት ነገር አንዳልሆነ ገልጻለች።

ከቤተሰብ ስለነበረባቸው ጫና ስታስረዳም '' በልጅነት አእምሮ አስባችሁት ነው፤ በኋላ ይቆጫችኋል'' ተብለው እንደነበር ትናገራለች።

ብዙ የቤተሰብ አባላትና ዘመድ አዝማዶችም እኛ እንረዳችኋለን፤ ወጪውን በእኛ ጣሉት የሚል ሃሳብ ቢያቀርቡም ኦልያድ እና ቢፍቱ ግን አሻፈረኝ በማለት የሚያስቡትን አይነት ሰርግ ማከናወን ችለዋል።