ቻይና ቅጥ ያጡ ሰርጎችን ልትቆጣጠር ነው

ቻይናውያን ሙሽሮች

የፎቶው ባለመብት, China Photos

የምስሉ መግለጫ, ቻይናውያን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ጠርተው ቅንጡ ሰርጎችን መደገስ ባህል እያደረጉት መጥተዋል

የቻይና ባለስልጣናት እጅግ የተጋነነ ወጪ የሚደረግባቸውና አንዳንዴም አላስፈላጊ ተግባራት የሚፈጹሙባቸው ሰርጎችን ለማስቀረት ጥረት እያደረጉ ነው ተብሏል።

እንደ ባለስልጣናቱ ከሆነ ዘመነኛ የሚባሉት ሰርጎች ከቻይናውያን ባህል ከማፈንገጣቸው በተጨማሪ አላስፈላጊ ወጪም ይወጣባቸዋል።

በባለስልጣነቱ እንደ መፍትሄ የቀረበው ሀሳብ ደግሞ ለሰርጎች የሚሆን የመመሪያ ሰነድ ማዘጋጀትና ስነስርአቶቹ ባህላዊውን የቻይና ስርአት የተከተሉ እንዲሆኑ ማድረግ ነው።

አሁን አሁን በመላው ዓለም እየተስተዋለ እንዳለው፤ ቻይናውያንም በሰርግ ድግሶቻቸው ወቅት ከቤተሰብ፣ ጎረቤት እንዲሁም ከጓደኞቻቸው የተሻሉ መሆናቸውን ለማሳየት ከፍተኛ ወጪ ለድግስ ከማውጣት እስከ ዓለምን መዞር የደረሱ ተግባራትን ይፈጽማሉ።

ይሄ ደግሞ በሚሊዮን ዶላሮች ከፍሎ ድግሱን ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ውስጥ ማዘጋጀት፣ ከቻይና ውጪ ተጉዞ የሰርግ ፎቶዎችን መነሳት እንዲሁም አውሮፕላን መከራየትን ያካትታል።

የሰርጉ ታዳሚዎችም ቢሆኑ ውድ ውድ ስጦታዎችን የማምጣት ግዴታ አለባቸው።

እነዚህ ሁሉ ነገሮች ተካተውበት የሚደገሰው የሰርግ ስነ-ስርዓት ደግሞ ሌላ አሳሳቢ ባህልም ተጨምሮበታል።

ሙሽሮቹን በሰርጋቸው ዕለት ዘና እንዲሉ ለማድረግ በማሰብ ቤተሰቦችና የቅርብ ጓደኞች ሙሽሮቹን ማስደንገጥን የመሳሰሉ የተለያዩ መንገዶችን ይጠቀማሉ።

ታዲያ እነዚህ ተግባራት ከማስደንገጥ አልፈው እስከ ማዋረድና አደጋ እስከ ማደረስ ደርሰዋል።

በቻይና ባህላዊ ስነስርአት የሚጋቡ ሙሽሮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ባለፈው ሳምንት እንኳ በተደረገ የሰርግ ስነ-ስርዓት ጓደኞቹ ከወንበር ጋር አስረው ሲገርፉት የነበረ ሙሽራ ለማምለጥ ሲሞክር በመኪና ተገጭቶ ከባድ ጉዳት ደርሶበታል።

በሌላ አጋጣሚ ደግሞ የወንድ ሙሽራ ሚዜዎች ሙሽሪት ያረፈችበትን ክፍል መስኮት በመጥረቢያ ሰብረው ለመግባት ሲሞክሩ የመስታወት ስባሪ ያገኛቸው ሚዜዎች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል ሄደው ነበር።

አንዳንዴም ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ ይሆኑና ሴት ሚዜዎች ጾታዊ ትንኮሳ ይደርስባቸዋል።

ጉዳዩ ያሳሰበው የቻይናው የሲቪል ጉዳዮች ሚኒስትር መስሪያ ቤት ደግሞ ያለአግባብ የሚወጡ ወጪዎችን ለመቀነስና የሃገሪቱን ባህል ለመታደግ በማሰብ አዲስ መመሪያ አዘጋጅቷል።

''የሰርግ ስነ-ስርዓቶች የቻይናን ሶሻሊስት አስተሳሰብና የቀድሞ ባህል ባስጠበቀ መልኩ ለማካሄድና ዘመን አመጣሽ የቅንጦት አስተሳሰቦችን ለመዋጋት አዲሱ መመሪያ ይረዳል'' ብሏል መስሪያ ቤቱ።

በቅርቡም ለሰርግ ስነ-ስርዓቶች የሚወጣውን ገንዘብ መጠን የሚወስንና የሰርጉን አጠቃላይ አካሄድ የሚቆጣጠረው መመሪያ ተግባራዊ ያደረጋል ተብሏል።