በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተሞሸሩት ጥንዶች

የፎቶው ባለመብት, የኢትዮጵያ ኤምባሲ
እሁድ ሚያዝያ 20፣ 2011 ዓ. ም. መሀመድ ጣሂርና አሲያ አብዱጀሊል ባልተለመደ መልኩ በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቅጥር ግቢ ውስጥ ተሞሽረዋል። ጥንዶቹ ኤምባሲው ውስጥ የሰርግ ፎቶ ተነስተዋል። ኬክም ቆርሰዋል።
ሙሽራው መሀመድ ጣሂር በስደት ወደ ኬንያዋ መዲና ናይሮቢ ከመጣ 12 ዓመታት ተቆጥረዋል። በኬንያ በቆየባቸው ዓመታት እንደዚህ አይነት ነገር አጋጥሞት እንደማያውቅና እድለኛ ነኝ ብሎ እንደሚያምን ይናገራል።
ከሳምንታት በፊት የሰርግ ሥነ ስርአቱን በአንድ ኬንያ ውስጥ በሚገኝ የኢትዮጵያ ሬስቶራንት ውስጥ ለማድረግ በማሰብ ወደ ሬስቶራንቱ የሄደው መሀመድ፤ በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑትን አቶ መለስ አለምን እዛው እንዳገኛቸው ይናገራል።
''በቅርቡ ላገባ እንደሆነና የምሳ ግብዣውን በሬስቶራንቱ ላደርግ እንደሆነ ለአምባሳደሩ ስነግራቸው፤ ለምን በኤምባሲው ቅጥር ግቢ ውስጥ ሰርጋችሁን አትፈጽሙም አሉኝ። ሙሉ ወጪውን ኤምባሲው እንደሚሸፍንም ነግረውኝ ነበር'' ይላል።
''ለምሳ ግብዣው አስቀድመን ስለከፈልን የፎቶና ኬክ የመቁረስ ሥነ ስርአቱን በኤምባሲው ቅጥር ግቢ ውስጥ ማከናወን እንደምንችል አምባሳደሩ ነገሩኝ።''
በመላው ዓለም ወደ ስልሳ የሚደርሱ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች እንዳሉ የሚናገሩት በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ መለስ ዓለም፤ እስካሁን ድረስ በየትኛው ኤምባሲ ቅጥር ግቢ ውስጥ እንደዚህ አይነት ድግስ ተዘጋጅቶ እንዳልተመለከቱ ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, የኢትዮጵያ ኤምባሲ
በኤምባሲው የቅርብ ጊዜ ታሪክ ውስጥ ይህ አጋጣሚ የመጀመሪያው ነው ሊባል እንደሚችልም አምባሳደሩ ያስረዳሉ።
''በዜጎችና በኤምባሲዎች መካከል ያለው የሻከረ ግንኙነት ታሪክ ሆኖ የኤምባሲው ግቢ ውስጥ እንዲደግሱ በምንችለው መጠን ለማስተናገድ ሞክረናል።''
በናይሮቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ፤ ዜጎች ሰርግ ወይም መሰል መሰናዶ ሲኖራቸው 'የአዳራሹን ነገር በኛ ጣሉት' የሚል መልእክት ከሳምንታት በፊት አስተላልፎ እንደነበር የሚያስታውሱት አምባሳደሩ፤ የጥንዶቹ የሰርግ ሥነ ስርአት ለሌሎችም በር ከፋች ሊሆን እንደሚችል ያምናሉ።
''በኛ እምነት ዜጎች የማይገቡበትና የማይወጡበት ኤምባሲ ኦና ነው። ንብ የሌለው ቀፎ እንደማለት ነው። ዜጎች ሲደሰቱና ሲከፉም የሚመጡበት ኤምባሲ ማድረግ ያስፈልጋል። እኛ ደግሞ ለዚህ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርገናል።''
መሀመድ ጣሂርና አሲያ አብዱጀሊል የምሳ ዝግጅታቸውን ጨርሰው ወደ ኤምባሲው ሲሄዱ ኬክና የሚጠጣ ነገርም ተዘጋጅቶ ነበር የጠበቃቸው።
''እኛ የጠራናቸው 60 ሰዎች ቢሆኑም በኤምባሲው ቅጥር ግቢ ስንደርስ የኤምባሲው ሠራተኞችና ሌሎች ሰዎችም ተጨምረው ወደ 100 የሚደርሱ ሰዎች ተሰብስበው ነበር። እጅግ የደመቀ ሥነ ስርአት ነበር የተካሄደው። በጣም ደስ ብሎኛል።''
አምባሳደሩ ''ኢትዮጵያውያን መጥተው ሰርግ ደግሰው፤ ደስታቸውን ማየት፤ ህጻናት በኤምባሲው ግቢ ውስጥ ሲቦርቁ መመልከት በጣም ደስ ይላል'' ብለዋል።
''ይሄ የኢትዮጵያውያን ቤት ነው። ኢትዮጵያውያን ግብር ከፋዮች የሠሩት ቤት ነው። የኛ አባቶችና አያቶች ባወጡት ገንዘብ የተሠራ ግቢ ነው። ስለዚህ ኤምባሲው ጥቅም ላይ ውሏል ብለን እናስባለን" ይላሉ።












