ኮሮናቫይረስ፡ ፈረንሳይ ኮቪድ-19ን በመከላከል ግንባር ቀደም ለነበሩ ስደተኞች ዜግነት ልትሰጥ ነው

በፓሪስ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት የጤና ባለሙያዎች በሥራ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በፈረንሳይ በኮሮናቫይረስ መከላከል ላይ ተሰማርተው የነበሩ እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ለአገሪቱ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከግምት ገብቶ ዜግነት እንዲያገኙ እየተደረገ ነው።

የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ኮቪድ-19ን በመዋጋት ጥረት ውስጥ ግንባር ቀደም በመሆን የተሰለፉ ነዋሪዎችን በፍጥነት ለዜግነት እንዲያመለክቱ ጥሪ አቅርቧል።

እስካሁን ድረስ ከ700 በላይ ስደተኞች ዜግነት ያገኙ አልያም ለማግኘት በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ የደረሱ መሆናቸው ተገልጿል።

የፈረንሳይ ዜግነት ከተሰጣቸው ስደተኞች መካከል የጤና ባለሙያዎች፣ የጽዳት ባለሙያዎች እና የንግድ ሱቅ ባለቤቶች ይገኙበታል።

በመላው ዓለም ኮቪድ-19ን በመከላከል ረገድ ከፊት በመሆን ያገለገሉ ዜጎች ለኮሮናቫይረስ የመጋለጥ እድላቸው ሰፊ ሲሆን፣ በዚህም የተነሳ ዶክተሮችና ነርሶችን ጨምሮ በርካቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

በዓለማችን ላይ በኮሮናቫይረስ ክፉኛ ከተጠቁ አስር አገራት መካከል ፈረንሳይ አንዷ ስትሆን ከ2.5 ሚሊየን በላይ ዜጎቿ በቫይረሱ ሲያዙ 62 000 ደግሞ በዚሁ ተህዋሲ ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ለኮሮናቫይረስ መከላከል ግንባር ቀደም ለሆኑ ስደተኞች ዜግነት የመስጠት ወሬው የተሰማው በመስከረም ወር ላይ ነበር።

74 ስደተኞች የፈረንሳይ ፓስፖርት የተሰጣቸው ሲሆን 693 ሰዎች ደግሞ በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ናቸው ተብሏል።

እስካሁን ድረስ 2,890 ስደተኞች ማመልከታቸውም ታውቋል።

በአገር ውስጥ ሚኒስቴር የዜግነት ጉዳዮች ቢሮ " የጤና ባለሙያዎች፣ ሴት የጽዳት ሰራተኛ ፣ የሕጻናት ተንከባካቢዎች፣ የመደብር ሰራተኞች ለዜጎች ያላቸውን ታማኝነትና ቁርጠኝነት አስመስክረዋል። አሁን ደግሞ ብድር መመለስ ተራው የፈረንሳይ ነው" ብሏል።

ከዚህ ቀደም ለዜግነት ማመልከት የሚችሉት ስደተኞች በፈረንሳይ ለአምስት ዓመት በቋሚነት የኖሩ፣ ቋሚ ገቢ ያላቸው እና ከፈረንሳይ ሕዝብ ጋረ ተስማምተውና ተቻችለው መኖርን ያስመሰከሩ ብቻ ነበሩ።

ነገር ግን በኮሮናቫይረስ መከላከል ውስጥ ከፊት ከነበሩ ስደተኞች ከሆኑ ሁለት ዓመት መኖርና " መልካም ሥራቸው የተመሰከረላቸው" መሆናቸው ብቻ በቂ ነው ተብሏል።

በ2017 የፈረንሳይ ስደተኞች ቁጥር 6.4 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን ዜግነት የማግኘት ሂደቱ ግን እጅጉን ዘገምተኛ ነበር ተብሏል።

ዜግነት የተሰጣቸው ስደተኞች ቁጥርም ሲታይ እኤአ በ2018፣ በ2019 የተሰጣቸው ስደተኞች በ10 በመቶ ቀንሰዋል።

ፈረንሳይ ማሊያዊ ስደተኛ አንድ ጨቅላን ከፎቅ እንዳይወድቅ በመታደጉ መልካም ስራውን በማድነቅ ዜግነት የሰጠችው በ2018 ነበር።