ኮሮናቫይረስ፡ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወደ አህጉረ አንታርክቲክ መዛመቱ ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከቫይረሱ ነጸ ሆኖ ወደቆየው አህጉረ አንታርክቲክ መዛመቱ ተሰማ።
የቺሊ ጦር አንታርክቲክ በሚገኘው በቤርናርዶ ኦ ሂጂን የምርምር ማዕከል 36 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸውን አስታውቋል።
በወረርሽኙ ከተያዙት 36 ሰዎች መካከል 26ቱ ወታደሮች፤ አስሩ ደግሞ የጥገና ሠራተኞች መሆናቸው ተገልጾ ለሕክምና እና ለክትትል ወደ ቺሊ መወሰዳቸው ተነግሯል።
ይህ ዜና የተሰማው የቺሊ የባሕር ኃይል ቁሳቁስና ሰዎችን ጭኖ ወደ ምርምር ማዕከሉ በወሰደው መርከብ ላይ በቫይረሱ የተያዙ ሦስት ሰዎች መገኘታቸውን ካስታወቀ ከቀናት በኋላ ነው።
ይህ ዜና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሁሉም የዓለማችን ሰባት አህጉሮች መግባቱን አረጋግጧል።
'ሳርጌንቶ አልዲያ' የሚል ስያሜ የተሰጣት መርከብ፤ በምርምር ማዕከሉ የደረሰችው ኅዳር 27 ሲሆን ወደ ቺሊ የተመለሰችው ደግሞ ታህሳስ 10 ነበር።
ሦስቱ የመርከቡ ሠራተኞች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው የተረጋገጠው ታልካሁዋኖ ወደሚገኘው የቺሊ የባሕር ኃይል ካምፕ ሲመለሱ ነው።
የቺሊ የባሕር ኃይል ወደ አንታርክቲክ ተሳፍረው የነበሩት በሙሉ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ተደርጎላቸው ሁሉም ከቫይረሱ ነፃ ነበሩ ተብሏል።
የበርናርዶ ኦ ሂጊንስ የምርምር ማዕከል ቺሊ በአንታርክቲክ ካላትና በጦር ሠራዊቱ ከሚተዳደሩ አራት ቋሚ ካምፖች ውስጥ አንዱ ነው።
ቺሊ በቫይረሱ ክፉኛ በመጠቃት በላቲን አሜሪካ ከሚገኙ አገራት በስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
እስካሁንም ከ585 ሺህ በላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ተመዝግበውባታል።












