ኮሮናቫይረስ፡ በፈረንሳይና በዩናይትድ ኪንግደም ድንበር ላይ የከባድ መኪኖች እንቅስቃሴ ተገታ

የፎቶው ባለመብት, PA Media
ከአንድ ሺህ አምስት መቶ በላይ ከባድ ጭነት መኪኖች ዩናይትድ ኪንግደምን ለቆ ለመውጣት የፈረንሳይ ድንበር ለንግድና ለጉዞ እስኪከፈት ድረስ በኬንት ከተማ መቆማቸው ተገለፀ።
ፈረንሳይ አዲሱን የኮሮናቫይረስ ዝርያ በመፍራት ከእሁድ ዕለት ጀምሮ ለ48 ሰዓታት ድንበሯን ዘግታለች።
በአሁኑ ሰዓት ከ50 በላይ አገራት ከዩናይትድ ኪንግደም የሚመጡ ተጓዦች ወደ አገራቸው እንዳይገቡ ከልክለዋል።
የከባድ መኪና አሽከርካሪዎቹ እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ የተለያዩ መፍትሔዎች እየታሰቡ ሲሆን አንደኛው አሽከርካሪዎቹ የኮቪድ-19 እንዲመረመሩ ማድረግ ነው ተብሏል።
ይህ በእንዲህ እዳለ የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን አገራት የጣሉት የጉዞ ገደብ እንዲያነሱ ጠይቋል።
ለአውሮፓ አባል አገራት በቀረበ ምክረ ሃሳብ ላይ የአውሮፕላን እና የባቡር ጉዞ ላይ የተጣለው ገደብ የአቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠር በሚል እንዲነሳ ተጠይቋል።
ነገር ግን ኮሚሽኑ እንዳለው ከሆነ አስፈላጊ ያልሆኑ ጉዞዎች አሁንም ቢሆን መበረታታት የለባቸውም።
የአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት በሙሉ አዲሱን ቫይረስ በመፍራት ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ሆነ ከአገሪቱ የሚደረጉ ጉዞዎችን አቋርጠዋል።
የአውሮፓ ሕብረትም የተባበረ ምላሽ መስጠት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እየመከረ ይገኛል።
በአሁኑ ጊዜ ወደ ፈረንሳይ ከዶቨር ወደብም ሆነ ከዩሮታነል የሚነሳ ተሽከርካሪ የለም።
የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ ፕሪቲ ፓቴል እንዳሉት ከሆነ 650 ከባድ የጭነት መኪኖች በኤም 20 እንዲሁም ተጨማሪ 873 ደግሞ በከባድ ተሽከርካሪዎች ማቆሚያ ስፍራ ይገኛሉ።
የአውሮፓ አገራት ድንበሮቻቸውን የዘጉት አዲሱ አይነት ቫይረስ መከሰቱን እና በፍጥነት መስፋፋቱን የዩናይትድ ኪንግደም ከፍተኛ ተመራማሪ ካስጠነቀቁ እና "በየትኛውም ስፍራ" እንደሚገኝ ካሳወቁ በኋላ ነው።
ሰር ፓትሪክ ቫላንስ አክለውም በእንግሊዝ ተጨማሪ ክልከላዎች ያስፈልጋል ብለዋል።

በእንግሊዝ 17 ሚሊዮን ሰዎች በጥብቅ የኮቪድ-19 ክልከላ ውስጥ ናቸው። ደረጃ አራት የእንቅስቃሴ ገደብ ከተጣለባቸው አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ሰዎችም በዌልስና በተወሰኑ የእንግሊዝ ከተሞች ሲደርሱ ራሳቸውን አግልለው እንዲቀመጡ ተደንግጓል።
ፓቴል እንዳሉት የተስተጓጎለውን የተሽከርካሪዎቹን እንቅስቃሴ ለማስቀጠል በዩናይትድ ኪንግደም እና በፈረንሳይ መካከል "መፍትሔ ለመፈለግ" ንግግሮች እየተደረጉ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን እና የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማርኮን ሰኞ ዕለት የተነጋገሩ ሲሆን እንደመፍትሔ ከዩናይትድ ኪንግደም ወደ ፈረንሳይ የሚመጡ አሽከርካሪዎች ተመርምረው ከኮቪድ-19 ነጻ መሆናቸው መረጋገጥ አለበት ብሏል።
ፓቴል የከባድ መኪና ሾፌሮቹን ኮሮናቫይረስ መመርመር "የንግግሩ አካል ነበር" ካሉ በኋላ "የምርመራ ውጤቱን በፍጥነት ማግኘትና ጉዞን ማቀላጠፍ በአንጻራዊነት ፈጣን ነው" ብለዋል።
በቦሪስ ጆንሰን እና በማርኮን የተደረሰው ስምምነት ከረቡዕ ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል።
በዩሮ ታነል ኃላፊዎች ማክሰኞ እለት 2500 የጭነት ተሽከርካሪዎች እንዲሁም ተመሳሳይ ቁጥር ያለው መኪና ረቡዕ ዩናይደትድ ኪንግደም ይደርሳሉ ብለው እንደሚገምቱ ተናግረዋል።
የድንበር መዘጋቱ በአውሮፕላን፣ በመርከብ እንዲሁም በባቡር ከዩናይትድ ኪንግደም ወደ ፈረንሳይ የሚጓዙ መንገደኞችን አስተጓግሏል።
ዩሮታነል እንዳለው ከዩናይትድ ኪንግደም ወደ ፈረንሳይ የሚሄዱ መንገደኞች ስምምነት ላይ ከተደረሰ ረቡዕ እና ሐሙስ መፍትሔ ሊያገኙ ይችሏሉ።
የብሪታንያ አየር መንገድም በአነስተኛ ቁጥር በረራ እንደሚጀምር አስታውቋል።













