ኮሮናቫይረስ፡ በርካታ የአውሮፓ አገራት በታላቋ ብሪታኒያ ላይ የጉዞ እቀባ እያደረጉ ነው

የፎቶው ባለመብት, PA Media
በርካታ የአውሮፓ አገራት በታላቋ ብሪታኒያ ላይ የጉዞ እቀባ እያደረጉ ነው። ምክንያቱ ደግሞ በዚያች አገር አዲስ ዓይነት የኮቪድ ዝርያ መገኘቱ ነው።
አዲሱ ዝርያ ገና በስፋት ያልተጠና ቢሆንም ከቁጥጥር ውጭ በሆነ መንገድ ከሰው ወደ ሰው ይዛመታል የሚለው ፍርሃት በርካታ አገራትን ድንጋጤ ውስጥ ከቷቸዋል።
እስከ አሁን ባለው ብቻ ጀርመን፣ አየርላንድ፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያንና ኔዘርላንድስ እንዲሁም ቤልጂየም ሁሉም ወደ ታላቋ ብሪታኒያ የአየር በረራን አቋርጠዋል።
ዛሬ ሰኞ የአውሮፓ ኅብረት መሪዎች ስብሰባ ስለሚቀመጡ ከዚህ የባሰ የእቀባ ውሳኔ ሊኖር እንደሚችል እየተጠበቀ ነው።
አዲሱ ኮቪድ-19 ዝርያ በለንደንና በደቡብ ምሥራቅ ኢንግላንድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ነው በስፋት የተሰራጨው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ቅዳሜ በሰጡት አስቸኳይ ትእዛዝ ደረጃ 4 የጥንቃቄ ደንቦች እንዲከበሩ አዘዋል። ለፈረንጆች ገናና አዲስ ዓመት የእንቅስቃሴ ገደቦች ይላላሉ ተብሎ ታስቦ የነበረውን ሐሳብ ሰርዘዋል።
የጤና ባለሙያዎች አዲሱ የተህዋሲው ዝርያ ይበልጥ ገዳይ ስለመሆኑም ሆነ ለክትባት እጅ የማይሰጥ ስለመሆኑ ገና እርግጠኛ አልሆኑም። ሆኖም ግን ከለመድነው የኮሮናቫይረስ በ70 በመቶ በይበልጥ የመሰራጨት አቅም አለው መባሉ ማን ይተርፋል እንዲባል አድርጓል።
የታላቋ ብሪታኒያ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ይህ አዲስ ዝርያ ቫይረስ ከቁጥጥር ውጭ ሆኖብናል፤ በቁጥጥራችን ልናውለው ይገባል ብለዋል።
ታላቋ ብሪታኒያ አዲሱን የቫይረስ ዝርያ ይፋ ባደረገች በሰዓታት ውስጥ ኔዘርላንድ ማንኛውም በረራ ከታላቋ ብሪታኒያ እንዳይመጣብኝ ብላለች።
ፈረንሳይ በተመሳሳይ ከባድ መኪና ተሽከርካሪ፣ መርከብ፣ ጀልባዎች፣ እግረኛና በበራዎችን ከእንግሊዝ በኩል ወደ አገሯ እንዳይገቡብኝ ብላለች። አየርላንድና ጀርመንም ተመሳሳይ ውሳኔን አሳልፈዋል።
ጣሊያን እስከ ጃንዋሪ 6 ማንም ከታላቋ ብሪታኒያ አይምጣብኝ ብላለች።
በአዲሱ የቫይረስ ዝርያ የተጠቃ አንድ ሰው በጣሊያን መገኘቱም ድንጋጤን ፈጥሯል።
ቱርክ፣ ቡልጋሪያና ኦስትሪያም ከታላቋ ብሪታኒያ ጉዞ እቀባ አድርገዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት አዲሱን የኮሮናቫይረስ ዝርያ በተመለከተ ከዩናይትድ ኪንግደም ባለሥልጣናት ጋር በቅርበት እየተነጋገረ እንደሆነ በትዊተር ገጹ አስታውቋል።
ድርጅቱ እንዳለው ዩናይትድ ኪንግደም አዲሱን የቫይረስ ዝርያ በተመለከተ እየተካሄዱ ስላሉ ጥናቶች መረጃዎችን ስታጋራ እንደነበር ጠቅሶ፤ ድርጅቱ ስለአዲሱ ቫይረስ ባሕርይ እና አደጋው የደረሰበትን ለአባል አገራቱ እና ለሕዝብ እንደሚያሳውቅ ገልጿል።
ምንም እንኳን የተረጋገጠ ነገር ባይኖርም፤ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን አዲሱ የቫይረስ ዝርያ ከቀድሞው እስከ 70 በመቶ ያህል የመዛመት እድሉ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ይሁን እንጂ ባለሥልጣናት አዲሱ የቫይረስ ዝርያ ከፍተኛ ሞት ስለማስከተሉ አሊያም እስካሁን በተዘጋጁት የኮሮናቫይረስ ክትባቶች እና ሕክምናዎች ሊበገር ስለመቻሉ የሚያሳይ መረጃ እንደሌለ ተናግረዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ ፋይዘርና በባዮንቴክ የበለጸገውን የኮሮናቫይረስ ክትባት ለዜጎቻቸው መስጠት መጀመራቸው ይታወሳል።
95 በመቶ ኮሮናቫይረስን ይከላከላል የተባለለት ይህንን ክትባት ለዜጎች በመስጠት ዩናይትድ ኪንግደም ቀዳሚዋ አገር ሆና ነበር።












