ኮሮናቫይረስ፡ በቱርክ የኦክስጅን ቬንትሌተር ፈንድቶ የኮሮና ህሙማንን ገደለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቱርክ በሚገኝ የኮሮናቫይረስ ህሙማን ማዕከል የኦክስጅን ቬንትሌተር ፈንድቶ ዘጠኝ የኮሮና ህሙማንን ገድሏል።
አደጋው ያጋጠመው ጋዚንቴፕ በምትባለው ግዛት የሚገኘው የሳንኮ ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል ነው። የቬንትሌተሩም መፈንዳትም በፅኑ ህሙማኑ ክፍል ውስጥ እሳት ማስነሳቱንም የአካባቢው ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
አንደኛው ህመምተኛም ወደ ሌላ ሆስፒታል ሊዛወር ሲል ነው የሞተው ተብሏል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ጀምሮ 2 ሚሊዮን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የተመዘገቡ ሲሆን 17 ሺህ 610 ሰዎችም ህይወታቸውን ማጣታቸውን ከጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
ፍንዳታው ባስከተለው እሳት የደረሰ ጉዳት እንደሌለም ሪፖርት የተደረገ ሲሆን ወዲያውም እሳቱን ለማጥፋት ርብርብ ተደርጓል።
ሟቾቹ ከ56-85 እድሜ የሚገመቱ መሆኑንም ከሆስፒታሉ የወጣው መግለጫ ያሳያል።
የኦክስጅን ቬንትሌተር ፍንዳታው እንዴት ተከሰተ ለሚለውም ምርመራ ተከፍቷል።
በፅኑ ህሙማን የሚገኙ በርካታ ሌሎች ህመምተኞችም አቅራቢያው ወደሚገኝ ሆስፒታልም ህክምና እንዲያገኙ መወሰዳቸውንም የጋዚያንቴፕ አስተዳደር ቢሮ በመግለጫው ጠቅሷል።
"ባለስልጣናቱ የሚያስፈልገውን እርምጃም እየወሰዱ ነው" ብሏል መግለጫው።
አክሎም በሞቱ ህይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች፣ ወዳጅ፣ ዘመዶች መፅናናትን ተመኝቷል።
የቱርክ ፕሬዚዳንት ኢብራሒም ካሊን ቃለ አቀባይም በትዊተር ገፃቸው "ለቆሰሉት በቶሎ እንዲያገግሙ እንመኛለን" በማለት ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።
በባለፈው ወር እንዲሁ በሮማንያ በተነሳ እሳት 10 የኮሮናቫይረስ ህሙማን ህይወታቸው አልፏል።
ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ለእሳቱ መነሻ የሆነው አንድ የህክምና ቁሳቁስ በእሳት ተያይዞ አቅራቢያ የነበረውን የኦክስጅን ሲሊንደር በማቀጣጠሉ ነው።
በጥር ወርም እንዲሁ በሩሲያዋ ቼልያቢንስክ ግዛት በሚገኝ ጊዜያው የኮሮናቫይረስ ሆስፒታል ውስጥ የኦክስጅን ክፍሉ ውስጥ ፍንዳታ በመነሳቱ እሳት አስከትሏል።
በቦታው የነበሩ 150 የኮሮናቫይረስ ህመምተኞችም በአስቸኳይ እንዲወጡ መደረጋቸውንም የሩሲያ ድንገተኛና አስከቸኳይ ሚኒስቴር ገልጿል።












