ኮቪድ-19፡ የቡሩንዲ የቀድሞ ፕሬዚዳንት በኮሮናቫይረስ ህይወታቸው አለፈ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የቡሩንዲ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ፒየር ቡዮያ በኮሮናቫይረስ ህይወታቸው ማለፉን የአጎታቸው ልጅና የዲፕሎማቲክ ምንጮች ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
የ71 አመቱ የቀድሞ መሪ በፓሪስም ህይወታቸው እንዳለፈ ተገልጿል።
በመፈንቅለ መንግሥት ወደ ስልጣን የመጡት ፕሬዚዳንት ቡሩንዲን ለ13 አመታትም ያህል መርተዋል።
በዚህም አመትም ጥቅምት የቡሩንዲ ፍርድ ቤት የመፈንቅለ መንግሥቱ ጉዳይ ላይ በተመሰረተ ክስ በሌሉበት የእድሜ ልክ እስራት ፈርዶባቸው ነበር።
ፍርድ ቤቱ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ለመጀመሪያ ጊዜ፣ በጎሮጎሳውያኑ 1993 የተመረጡትን ፕሬዚዳንት ሜልቾይር ናዳየን ገድለዋቸዋልም በሚል ነው ብያኔውን ያስተላለፈው። በወቅቱም 300 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች ህይወት ተቀጥፏል።
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግን ምንም አይነት ስህተት አልፈፀምኩም በማለት ክደዋል።
በአፍሪካ ህብረት የሳህልን ቀጠና ወክለው ልዩ መልዕክተኛ የነበሩ ሲሆን ባለፈውም ወር ነው ከዚሁ ኃላፊነታቸው የለቀቁት፤ ንፁህነታቸውንም ለማስመስከር እስከ መጨረሻ ድረስ እታገላለሁም በማለት ፀንተው ነበር።










