ኮቪድ-19፡ የቺሊው ፕሬዚደንት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ 'ሰልፊ' በመነሳታቸው ተቀጡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ደቡብ አሜሪካዊቷ አገር ቺሊ ፕሬዚደንት ሴባስቲያን ፒኔራ የኮሮናቫይረስ ሕግን በመጣሳቸው 3 ሺህ 500 ዶላር ገንዘብ ተቀጡ።
ፕሬዚደንቱ ቅጣቱ የተጣለባቸው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ 'ሰልፊ' በመነሳታቸው ነው።
ሰባስቲያን በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ይኸው ከአንዲት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ካላደረገች ሴት ጋር የተነሱት ፎቶ በስፋት ከተሰራጨ በኋላ ይቅርታ ጠይቀዋል።
ፕሬዚደንቱ በካቻጓ በሚገኘው ቤታቸው አቅራቢያ ባለ የባህር ዳርቻ ሴትዮዋ አብረዋት ፎቶ እንዲነሱ ስትጠይቃቸው "የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ነበረብኝ" ብለዋል።
ቺሊ ሕዝብ በሚገለገልባቸው ቦታዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግን የሚያዝ ጥብቅ ሕግ አላት።
ይህንን ሕግ መጣስም የገንዘብና የእስር ቅጣትን ጨምሮ ሌሎች ቅጣቶችን ያስከትላል።
ፕሬዚደንቱ በተለያዩ ጊዜ የሚነሷቸው አነጋጋሪ ፎቶግራፎች ፖለቲካዊ መዘዝ እያስከተሉ ነው።
ባለፈው ዓመት በዋና መዲናዋ ሳንቲያጎ እኩልነትን የሚጠይቅ ተቃውሞ በተካሄደ ምሽት በአንድ የፒዛ ድግስ ላይ ፎቶ በመነሳታቸው ቁጣ አስነስቶ ነበር።
በዚያው ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ገደብ ሳይጣል በፊት ፀረ- መንግሥት ተቃውሞ ማዕከል በነበረ አደባባይ ፎቶ በመነሳታቸው በርካቶችን አስቆጥቷል።
በሳንቲያጎ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የተጣሉ ገደቦችን ተከትሎ አለመረጋጋቶች ተከስተዋል።
ከሰኔ ወር ወዲህም በአንድ ቀን ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች በኮሮናቫይረስ እየተያዙ ነው።
በታህሳስ ወር መጀመሪያ ላይ ፕሬዚደንቱ ሌሎች በሽታውን ለመቆጣጠር የተጣሉ ገደቦች እንዲቀጥሉ የሚያስችለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለ3 ወራት አራዝመዋል።
በቺሊ የኮሮናቫይረስ ሥርጭት እየጨመረ ሲሆን በላቲን አሜሪካ በበሽታው የተያዙና የሞቱ ሰዎች ከፍተኛ ቁጥር ከተመዘገበባቸው አገራት አንዷ ናት ።
እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ በአገሪቷ እስካሁን 581 ሺህ 135 ሰዎች በቨይረሱ የተያዙ ሲሆን 16 ሺህ 051 ሰዎች ደግሞ በበሽታው ሕይወታቸው አልፏል።












