ኮቪድ-19፡ የዓለም ጤና ድርጅት በዩኬ የተከሰተውን አዲሱን የኮሮናቫይረስ ዝርያ በቅርበት እየተከታተልኩ ነው አለ

ክትባት እየተከተበች ያለች ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የዓለም ጤና ድርጅት በዩናይትድ ኪንግደም የተከሰተውን አዲስ የኮሮናቫይረስ ዝርያ በተመለከተ ከአገሪቷ ባለሥልጣናት ጋር በቅርበት እየተነጋገረ መሆኑን አስታወቀ።

የአገሪቷ ባለሥልጣናት እንዳሉት አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ቀድሞ ከነበረው በበለጠ በስፋት እየተዛመተ ሲሆን፤ የበለጠ ገዳይ ነው ተብሎ ግን አይታመንም።

ለንደንን ጨምሮ የደቡብ ምስራቅ እንግሊዝ ሰፊው ክፍል የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት አዲስ እና ጥብቅ ገደብ ውስጥ ናቸው።

ኔዘርላንድስ አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ መከሰትን ተከትሎ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የሚደረጉ በረራዎችን ማገዷን አስታውቃለች።

እገዳው ከእሁድ ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን እስከ አውሮፓውያኑ ጥር አንድ ድረስ እንደሚቆይ የደች መንግሥት ገልጿል።

እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በዩናይትድ ኪንግደም ከተገኘው አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ናሙና በመገኘቱ እንደሆነ ተነግሯል።

በዩኬ የተከሰተውን ሁኔታ የበለጠ ግልፅ እንዲሆን እየተጠባበቁ መሆኑን የገለፀው የአገሪቷ መንግሥት፤ "አዲሱ የቫይረስ ዝርያ ወደ ኔዘርላንድስ ሊገባ የሚችልበትን ሁኔታ በተቻለ መጠን መገደብ አለበት" ብሏል።

የደች መንግሥት አክሎም በቀጣዮቹ ቀናት በዩኬ የተገኘውን የአዲሱን ቫይረስ አደጋ ባለበት ለመቆጣጠር ስለሚያስችለው ሁኔታ ከሌሎች የአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት ጋር አብሮ እንደሚሰራ አስታውቋል።

ስለአዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ የምናውቀው

የዓለም ጤና ድርጅት አዲሱን የኮሮናቫይረስ ዝርያ በተመለከተ ከዩኬ ባለሥልጣናት ጋር በቅርበት እየተነጋገረ እንደሆነ በትዊተር ገጹ አስታውቋል።

ድርጅቱ እንዳለው ዩኬ አዲሱን የቫይረስ ዝርያ በተመለከተ እየተካሄዱ ስላሉ ጥናቶች መረጃዎችን ስታጋራ እንደነበር ጠቅሶ፤ ድርጅቱ ስለአዲሱ ቫይረስ ባሕርይ እና አደጋው የደረሰበትን ለአባል አገራቱ እና ለሕዝብ እንደሚያሳውቅ ገልጿል።

ምንም እንኳን የተረጋገጠ ነገር ባይኖርም፤ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን አዲሱ የቫይረስ ዝርያ ከቀድሞው እስከ 70 በመቶ ያህል የመዛመት እድሉ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

ይሁን እንጂ ባለሥልጣናት አዲሱ የቫይረስ ዝርያ ከፍተኛ ሞት ስለማስከተሉ አሊያም በበለጸጉት የኮሮናቫይረስ ክትባቶች እና ሕክምናዎች ሊበገር ስለመቻሉ የሚያሳይ መረጃ እንደሌለ ተናግረዋል።

ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ ፋይዘርና በባዮንቴክ የበለጸገውን የኮሮናቫይረስ ክትባት ለዜጎቻቸው መስጠት መጀመራቸው ይታወሳል።

95 በመቶ ኮሮናቫይረስን ይከላከላል የተባለለት ይህንን ክትባት ለዜጎች በመስጠት ዩናይትድ ኪንግደም ቀዳሚዋ አገር ሆና ነበር።