ኮሮናቫይረስ፡ አሜሪካ የሞደርና ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቀደች

ክትባት

የፎቶው ባለመብት, MODERNA

አሜሪካ ሞደርና ሰራሹ የኮቪድ ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል ፍቃድ ሰጠች።

ከአንድ ሳምንት በፊት የአሜሪካ የምግብ እና መድሃኒት ተቆጣጣሪ የፋይዘር/ባዮንቴክ ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል ፍቃድ መስጠቱ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎ የሞደርና ክትባት በአሜሪካ ጥቅም ላይ እንዲውል ፍቃድ ያገኘ ሁለተኛው ክትባት ሆኗል።

ባለስልጣናቱ 200 ሚሊዮን የሞደርና ክትባትን ለመገዛት ከስምምነት የደረሱ ሲሆን ከዚህም መካከል 6 ሚሊዮን የሚሆነው ለስርጭት ዝግጁ መሆኑ ተነግሯል።

አሜሪካ በቫይረሱ ክፉኛ ጉዳት ደረሰባት አገር ናት። እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ አሃዝ ከሆነ 313 ሺህ 500 ሰዎችን በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን ከ17.5 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ደግሞ በቫይረሱ ተጠቅቷል።

የምግብ እና መድሃኒት አስደተዳደር ኮሚሽነር ስቴፋን ሃን ሞደርና ሰራሹ ክትባት በአሜሪካ ጥቅም ላይ እንዲውል መፈቀዱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ያጠቃውን በሽታ ለመቆጣጠር ትልቅና ጉልህ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

ሞደርና ሰራሹ ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል ፍቃድ ያገኘው የአሜሪካ መንግሥት የጤና አማካሪ ቡድን ክትባቱ ጥቅም ላይ እንዲውል ፍቃድ እንዲሰጠው ምክረ ሃሳባቸውን ካቀረቡ በኋላ ነበር። የሞደርና ክትባት ደህንነቱ የተጠበቀ እና 94 በመቶ ሰዎችን ከበሽታ የመከላከል አቅም ያለው እንደሆነ ተጠቁሟል።

ፕሬዝደንት ትራምፕ በትዊተር ገጻቸው ላይ ክትባቱ ጥቅም ላይ እንዲውል ፍቃድ መሰጠቱን ገልጸው ክትባቱን የማከፋፈሉ ሥራ መጀመሩን አስታውቀዋል። “እንኳን ደስ ያላችሁ ሞደርና ክትባት አሁን ይገኛል!” ሲሉም ፕሬዝደንት ትራምፕ ጽፈዋል።

የፊታችን ሰኞ ክትባት እንደሚወስዱ የተገለጸው ተመራጩ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የፋይዘር/ባዮንቴክ እና ሞደርና ክትባቶች ጥቅም ላይ መዋላቸው ወደፊት የተሻለ ሕይወት እንደሚጠብቀን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

የሞደርና ክትባት ከፋይዘር በምን ይለያል?

ሁለቱ ክትባቶች የሚለዩበት አንድ መሠረታዊ ጉዳይ ሲከፋፈሉ እና ሲከማቹ የሚቆዩበት የቅዝቃዜ መጠን ነው።

የአሜሪካው ፋይዘር እና የጀርመኑ ባዮንቴክ የሰሩት ክትባት ሲጓጓዝም ሆነ ሲከማች የቅዝቃዜ መጠኑ ከዜሮ በታች 75 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በሆነ ስፍራ መቀመጥ ይኖርበታል። ይህም የሎጂስቲክ ስራውን ከባድ ያደርገዋል።

በሌላ በኩል የሞደርና ክትባት መከማቸት እና መጓጓዝ ያለበት ከዜሮ በታች 20 ዲግ ሴንቲግሬድ በሆነ ቅዝቃዜ ውስጥ ነው።

ሁለቱም ክትባቶች ሰዎች በቀናት ልዩነት ሁለት ጊዜ መውሰድ ይኖርባቸዋል።

ሞደርና ሰራሹ ክትባት ሁለት ጊዜ መወሰድ ያለበት በ28 ቀናት ልዩነት ሲሆን የፋይዘር/ባዮንቴክ ክትባት ግን በ21 ቀናት ልዩነት ነው።

ሞደርና ክትባቶቹን የሚያመርተው በአሜሪካ ማሳቹሴትስ ግዛት ነው። ፋይዘር በበኩሉ ክትባቱን የሚያመርተው ጀርመን እና ቤልጄም በሚገኙ ፋብሪካዎቹ ነው።

ካናዳ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ የአውሮፓ ሕብረት፣ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን የሞደርና ክትባት ለዜጎቻቸው እንዲሰጡ ውሳኔ ባያስተላልፉም ክትባቱን ለመግዛት ግን ቀድመው ውል አስረዋል።