ትግራይ ፡ የህወሓት አመራሮች ያሉበትን ለጠቆመ የ10 ሚልዮን ብር ሽልማት መዘጋጀቱ ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በመንግሥት እየተፈለጉ ያሉትን የህወሓት ከፍተኛ አመራሮችን ለመያዝ ጥቆማ ለሚሰጡ ሰዎች ከፍተኛ መጠን ያለው የገንዘብ ሽልማት መዘጋጀቱን ገለጸ።
በዚህም መሠረት አመራሮቹን ጠቁሞ በመንግሥት ቁጥጥር ስር እንዲውሉ የሚያስችል መረጃዎችን ለሚሰጡ ሰዎች የአስር ሚሊዮን ብር ሽልማት እንደሚሰጥ ቃል ገብቷል።
ይህ የገንዘብ ሽልማት መዘጋጀቱን ይፋ ያደረጉት የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት መረጃ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄነራል አስራት ዴኔሮ ሲሆኑ፤ ሽልማቱ ተፈላጊዎቹን አመራሮችን "በአጭር ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የተዘጋጀ ነው" ብለዋል።
ተፈላጊዎቹ ያሉበትን የሚያውቁ ሰዎች በየአካባቢያቸው ለሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በአካል በመቅረብ ማሳወቅ እንደሚችሉ የተነገረ ሲሆን፤ በተጨማሪም ለዚሁ አገልግሎት የሚውል የስልክ ቁጥር መዘጋጀቱም ተጠቁሟል።
ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኘው የአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት የሠሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ መንግሥት በህወሓት ኃይሎች ላይ ወታደራዊ ዘመቻ አካሂዶ የህወሓት አመራሮችን ከክልሉ የስልጣን መንበር ላይ ማስወገዱ ይታወሳል።
ወታደራዊ ዘመቻውን ተከትሎም የህወሓት ፖለቲካዊና ወታደረዊ ከፍተኛ አመራሮች ላይ የእስር ማዘዣ ወጥቶባቸው እየተፈለጉ መሆኑም አይዘነጋም።

የፎቶው ባለመብት, ENDF Facebook
ከእነዚህም መካከል በርካታ ወታደራዊ አመራሮች ተይዘው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ሲሆን፤ ከፖለቲካዊ አመራሮቹ መካከል አስካሁን ሁለቱ መያዛቸው ይታወቃል።
የቀድሞዋ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም ከሳምንታት በፊት እጃቸውን መስጠታቸው የተነገረ ሲሆን የቀድሞው የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና አምባሳደር የነበሩት አዲስዓለም ባሌማ ተይዘው ባለፈው ሳምንት ፍርድ ቤት መቅረባቸው ይታወሳል።
በትግራይ ክልል ውስጥ ለሦስት ሳምንታት ያህል ከተካሄደ ወታደራዊ ዘመቻ በኋላ ኅዳር 19/2013 ዓ.ም የፌደራል መከላከያ ሠራዊት የክልሉን ዋና ከተማ ከተቆጣጠረ በኋላ አብዛኞቹ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች የት እንዳሉ አይታወቅም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ መቀለ በሠራዊቱ መያዟን ተከትሎ ወታደራዊው ዘመቻ መጠናቀቁን የገለጹ ቢሆንም፣ ከስልጣናቸው የተባረሩት የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ግን ውጊያውን እንደሚቀጥሉ አሳውቀው ነበር።
ከመቀለ መያዝ በኋላ በነበሩት ጥቂት ቀናት ውስጥ የተወሰኑት የህወሓት አመራሮች ስለውጊያው ወቅታዊው ሁኔታ በቴሌቪዥንና በዜና ወኪሎች በኩል ካልተገለጹ ቦታዎች መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል።
በመገናኛ ብዙሃን ሲቀርቡ የነበሩትን የቀድሞውን የክልሉን ፕሬዝዳንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤልንና አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ ሌሎቹ ከፍተኛ የህወሓት አመራሮች አስካሁን ያሉበት ሥፍራም ሆነ ሁኔታ አይታወቅም።














