ፖሊስ ሜ/ጄ ጻድቃንን ጨምሮ ከ40 በላይ መኮንኖች ላይ የመያዣ ትዕዛዝ አወጣ

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አርማ

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Federal Police Commision

የፌደራል ፖሊስ በአገር ክህደት እና ትግራይ ውስጥ የመከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ አባላት እንዲታገቱ አድርገዋል ብሎ የጠረጠራቸውን ከአርባ በላይ የቀድሞ ከፍተኛ መኮንኖች ላይ የመያዣ ትዕዛዝ ማውጣቱን አስታወቀ።

ፖሊስ አርብ ምሽት ላይ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፤ የእስር ማዘዣው ቁጥራቸው ከአርባ በሚልቁ ከፍተኛ የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል፣ የመከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ አመራሮች መውጣቱን ገልጾ የተጠረጠሩትም በአገር ክደትና በሠራዊት አባላት ላይ በተፈጸመ ወንጀል ነው ብሏል።

የመያዣ ትዕዛዙ ከወጣባቸው ከፍተኛ መኮንኖች መካከል የቀድሞው የአገሪቱ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የነበሩት ሜጀር ጄኔራል ጻድቃን ገብረተንሳይ እንደሚገኙበት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።

በተጨማሪም ኮሎኔል በርሄ ወልደ ሚካኤልና ኮሚሽነር ይህደጎ ስዩምን ጨምሮ ሌሎቹም ጥቅምት 24/2013 ዓ. ም በትግራይ ክልል "በመከላከያ ሠራዊትና በፌዴራል ፖሊስ አባላት ላይ የተካሄደውን እገታ እንደመሩና እንዳስተባበሩ በምርመራ የተደረሰባቸው" መሆኑን የፌደራል ፖሊስ ገልጿል።

የመያዣ ትዕዛዙ የወጣባቸው ከፍተኛ መኮንኖች የተጠረጠሩበት ድርጊት በአገር ላይ ጥቃት ለመፈፀም በማቀድና በመሳተፍ መሆኑን አመልክቶ፤ ተፈላጊዎቹ ሠራዊቱን የከዱና በጡረታ የተገለሉ እንደሆነ መግለጫው አመልክቷል።

የፌደራል ፖሊስ አክሎም አሁን የመያዣ ትዕዛዝ የወጣባቸውንና ሌሎችን ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ወደ መቀለ ከተማ የኮማንዶና የወንጀል ምርመራ ቡድን አሰሳ እንደሚያደርግና ውጤቱንም ይፋ እንደሚያደርግ ገልጿል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ከአሁኑ የመያዣ ትዕዛዝ ቀደም ብሎ ኅዳር 9/2013 ዓ. ም ላይ በ76 ጄኔራሎች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የበታች ሹማምንቶች ላይ "ከህወሓት ጋር በመተባበር የአገር ክህደትን ፈፅመዋል" በሚል የእስር ትዕዛዝ እንደወጣባቸው ይታወሳል።

በህወሓትና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ለወራት የቆየው አለመግባባት በትግራይ ክልል በተናጠል የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ እየናረ በሄደበት ጊዜ አንደኛው ወገን ለሌላኛው የሕጋዊነት ዕውቅና በመንፈግ በተካረረ ውዝግብ ውስጥ ቆይተው ነበር።

ይህ ፍጥጫ ጥቅም 24/2013 ዓ. ም የህወሓት ኃይሎች በትግራይ ክልል በሚገኘው የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ካዘዙ በኋላ በሦስት ሳምንት ውስጥ የክልሉ ዋና ከተማ በመንግሥት ሠራዊት ቁጥጥር ስር መግባቷ ይታወሳል።

የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ አሁንና ከዚህ ቀደም በፌደራል ፖሊስ የመያዣ ትዕዛዝ ከወጣባቸው ወታደራዊና የፖሊስ መኮንኖች በተጨማሪ ዐቃቤ ሕግ በተለያዩ ከባድ ወንጀሎች በጠረጠራቸው የህወሓት አመራሮች ላይ ጭምር የእስር ማዘዣ አውጥቷል።

እስካሁን በቁጥጥር ስር የዋሉ ጦር ሠራዊትና የፖሊስ መኮንኖች የሚገኙ ሲሆን፤ ከህወሓት ፖለቲካዊ አመራሮች መካከል ደግሞ የቀድሞዋ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂምና የትግራይ ክልል የቀድሞ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አዲስዓለም ባሌማ (ዶ/ር) ይገኙባቸዋል።

የጦር ሠራዊትና የፖሊስ መኮንኖቹ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፤ አዲስዓለም ባሌማ (ዶ/ር) ለመጀመሪያ ጊዜ ፈርድ ቤት ቀርበው ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቆባቸዋል።