በአፍጋኒስታን በደረሰ ፍንዳታ የ15 ህጻናት ሕይወት አለፈ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በምስራቃዊ የአፍጋኒስታን ግዛት ጋዝኒ በደረሰ ፍንዳታ 15 ህጻናት ሲገደሉ 20 ሰዎች ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው ባለስልጣናትና የፖሊስ ምንጮች ገለጹ።
የፍንዳታው ምክንያት እስካሁን በትክክል ምን እንደሆነ ባይታወቀውም የአከባቢው ባለስልጣናት በሰዎች ጉልበት በሚጎተት የሰዎች ማመላለሻ ጋሪ ላይ ቦምብ ፈንድቶ ጉዳት ሳያደርስ አይቀርም ብለዋል።
የአከባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው ፍንዳታው የተከሰተው በመንደሩ የሚገኙ ህጻናት ተቀጣጣይ ነገር ለአንድ የመንገድ ላይ ቸርቻሪ ለመሸጥ ሲሞክሩ ነው ይላሉ።
የታሊባን ታጣቂዎችም ቢሆኑ ፍንዳታው ሆነተብሎ የተፈጸመ እንዳልሆነ አስታውቀዋል።
ፍንዳታው የተሰማው ትናንት ምሽት እኩለ ሌሊት አካባቢ ሲሆን በመንደሪቷ የሚገኙ ሰዎች በአንድ ቤት ውስጥ ተሰብስበው ቁርአን እየቀሩ ነበር።
ፍንዳታው ከመከሰቱ በፊት ሰዎች ማመለማለሻ ጋሪውን የሚያንቀሳቅሰው ግለሰብ ልክ ወደ መንደሪቱ ሲገባ ህጻናት ወዲያው ከከበቡት በኋላ ነው ሲሉ የጋዝኒ ግዛት አስተዳዳሪ ቃል አቀባይ ዋሂዱላህ ጁማዛዳ ለአሶሺየትድ ፕረስ ገልጸዋል።
አክለውም የሟቾች ቁጥር ከዚህም በላይ ከፍ ሊል እንደሚችል ገልጸዋል።
የፖሊስ ቃል አቀባዩ አህመድ ክሃን ደግሞ ጥቃቱን የፈጸመው ታሊባን ነው በማለት መወንጀላቸውን ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የታሊባን ቃል አቀባዩ ዛቢሁላህ በበኩላቸው የሟቾች ቁጥር 12 እንደሆነና ህጻናቱ ያመጡት ያልፈነዳ ቀለሃ ለአደጋው መንስኤ እንደሆነ ገልጸዋል።












