የሴቶች ጥቃት፡ ህንዳዊቷን በቡድን ደፍረው ገድለዋል የተባሉ አራት ሰዎች ክስ ተመሰረተባቸው

የተቆጡ ህንዳውያን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሕንድ የ19 ዓመት ወጣትን በቡድን ደፍረውና ገድለዋል የተባሉ አራት ግለሰቦች ክስ ተመሰረተባቸው።

ወጣቷ በአገሪቷ ሰሜናዊ ግዛት ኡታር ፕራዲሽ ጥቃቱ ከተፈፀመባት በኋላ ሆስፒታል ገብታ ነበር።

ይሁን እንጂ በደረሰባት ከፍተኛ ጉዳት ሳቢያ ሕይወቷ ሳይተርፍ ቀርቷል።

የአስራ ዘጠኝ አመቷ ታዳጊ በህንድ የማህበረሰብ አመዳደብ መሰረት ዝቅተኛ ስፍራ የተሰጣቸውና ዳሊት የሚባሉ ሲሆኑ በቀደመው ወቅትም የማይነኩ የማይባሉ ናቸው።

የደፈሯትም አራት ወንዶች ከላይኛው መደብ የሚመደቡ ናቸውም ተብሏል።

የወጣቷ ሞት በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በመላ አገሪቷ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ቁጣን ቀስቅሶ ነበር።

የዚህ ወንጀል ምርመራ የተያዘበት አግባብም በስፋት ሲተች ነበር። የአካባቢው ፖሊስ ሆነ ብሎ ጉዳዩን እያድበሰበሰ ነው የሚሉ ክሶችም ነበሩ።

ይህንን ተከትሎም ጉዳዩ ወደ ሕንድ ማዕከላዊ የምርመራ ቢሮ እንዲተላለፍ ተደርጓል።

አራቱ ተጠርጣሪዎች ወጣቷን በሃትራስ አካባቢ በሚገኝ ሜዳ ላይ ጥቃት በመፈፀም እንደደፈሯት ተገልጿል።

ከሁለት ሳምንታት በኋላም ሕይወቷ አልፏል።

ቤተሰብ ያለ ዕውቅናቸው ቀብሯ ተፈፅሟል በማለት ፖሊስን ወንጅለዋል፤ በህንድ የቀብር ባህል ስነ ስርአትም መሰረትም አስከሬኗን አቃጥለውታል ብለዋል።

ባለሥልጣናት ግን ይህንን አላደረግንም ሲሉ ክሱን አስተባብለዋል።

በቡድን መደፈሯና መገደሏ ሁኔታ በአገሪቷ በከፍተኛ ሁኔታ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን ያለ ቤተሰቦቿ እውቅና በዚህ መንገድ መቀበሯም "ኢሰብዓዊ ውሳኔ" ነው በማለት ተሟጋቾች ማውገዛቸው የሚታወስ ነው

አንድ የመንግሥት ባለሥልጣንም በተደረገ የአስክሬን ምርመራ የወንድ ፈሳሽ ባለመገኘቱ ወጣቷ እንዳልተደፈረች በመግለፅ፤ "ለሞት የተዳረገችውም በትንኮሳ ሳቢያ በተፈጠረባት ጭንቀት ነው" ሲሉ ተናግረው ነበር።

ከስምንት ዓመታት በፊት በደልሂ በአውቶብስ ውስጥ የተፈፀመ የመድፈር ወንጀልና ግድያ ዓለም አቀፍ ቁጣን መቀስቀሱ ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ በአገሪቷ የመድፈርና ወሲባዊ ጥቃት ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶታል። ይህም አገሪቷ የነበራትን የመድፈር ወንጀል ሕግ እንድትቀይር ምክንያት ሆኗል።

ይሁን እንጂ አሁንም በሴቶች ላይ የሚፈፀም ጥቃት አልቀነሰም።