ህንዳዊቷን ዶክተር በቡድን ደፍረው ገድለዋል ተብለው የተጠረጠሩት በፖሊስ ተገደሉ

ህንዳውያን በተቃውሞ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ከሰሞኑ በህንዷ ግዛት ሃይደራባድ አንዲት ዶክተር በቡድን ተደፍራ ተገድላ አስከሬኗ የተገኘ ሲሆን፤ ከግድያዋም ጋር ተያይዞ አራት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ነበር።

እነዚህን ተጠርጣሪዎች ፖሊስ ተኩሶ እንደገደላቸው ተዘግቧል።

በፖሊስ ቁጥጥር ስር የነበሩት ተጠርጣሪዎች በዚሁ ሳምንት አርብ እለት ወንጀሉ ወደተፈፀመበት ቦታ ተወስደው ነበር።

በቦታው ላይ እያሉ የፖሊስ ኃላፊዎቹን ጠመንጃ ሰርቀው ሊያመልጡ ሲል እንደተኮሱባቸውም ፖሊስ ለቢቢሲ ገልጿል።

ምንም እንኳን ፖሊስ ይህን ይበል እንጂ አምነስቲን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ሆን ተብሎ የተፈፀመ ግድያ ሊሆን ስለሚችል ምርመራ ሊደረግበት እንደሚገባ የህንድን መንግሥትን እየጠየቁ ነው።

"መደፈርን ለመከላከል መፍትሄው ግድያ አይደለም" በማለት በህንድ የአምነስቲ ስራ አስፈፃሚ አቪናሽ ኩማር ተናግረዋል።

የሃያ ሰባት አመቷ ዶክተር አስከሬኗ ተጥሎ የገኘው ከሰሞኑ ነው፤ ይህም ሁኔታ በሃገሪቷ ውስጥ ከፍተኛ ቁጣን መቀስቀሱ የሚታወስ ነው።

የተጠርጣሪዎቹ መገደል ከተሰማ በኋላ የሟች እናት ለቢቢሲ "በእውነቱ ፍትህን አግኝተናል" ያሉ ሲሆን፤ ጎረቤቶቻቸውም የተጠርጣሪዎችን መገደል ሲሰሙ በመንገድ ላይ ርችት በመተኮስ እንዲሁም ለፖሊስ ምስጋናቸውን በማሰማት ደስታቸውን ገልፀዋል።

ተጠርጣሪዎቹ አስከሬኗ ወደተገኘበትና ወንጀሉ ወደተፈፀመበት ቦታ ሲወሰዱ በአስር ፖሊሶች ታጅበው የነበረ ሲሆን፤ በካቴናም አልታሰሩም ነበር ተብሏል።

ተደፍራ የተገደለችበት አካባቢም ማይክሮሶፍትና ጉግልን ጨምሮ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ቢሯቸው የሚገኝበት ስፍራ ነው።

የፖሊስ ኮሚሽነሩ እንደገለፁት በወቅቱም ጠፋ የተባለውን የሟቿን ስልክ እየፈለጉ በነበረበት ወቅት ተጠርጣሪዎቹ በድንጋይና በዱላ ፖሊሶች ላይ ጥቃት ሲጀምሩ፤ በአፀፋው ሁለቱ ፖሊሶች እንደተኮሱባቸው ነው።

"ምንም እንኳን ፖሊሶቹ እጅ እንዲሰጡና ከጥቃቱ እንዲታቀቡ በተደጋጋሚ ቢያሳስቧቸውም፤ ለአስራ አምስት ደቂቃ ያህልም ፖሊሶቹን በማዋከባቸው ተኩሰው ገድለዋቸዋል" ብለዋል።

ሁለት ፖሊሶችም ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ሆስፒታል እየታከሙ እንደሆነ ኮሚሽነሩ አክለው ገልፀዋል።

"እውነት ለመናገር፤ ሕግ የማስከበር ስራ ተሰርቷል" ብለዋል።

የሟቿ ቤተሰቦች ልጃቸው ጠፍታ በነበረበት ወቅት ፖሊስ ፈጣን ምላሽ አልሰጠንም በማለት ተችቷቸው እንደነበር የሚታወስ ነው።