የ7 ዓመቷ ታዳጊ ሬስቶራንት ውስጥ መደፈሯ ደቡብ አፍሪቃውያንን አስቆጥቷል

የፎቶው ባለመብት, AFP
ደቡብ አፍሪቃውያን አንዲት የሰባት ዓመት ታዳጊ ሬስቶራንት ውስጥ ተደፍራለች መባሉን ተከትሎ ቁጣቸውን በመግለፅ ላይ ናቸው።
በአስገድዶ መድፈር የተጠረጠረው የ20 ዓመት ግለሰብ ወደ ሴቶች መፀዳጃ ቤት ተከትሏት በመግባት ልጅቱን ወደ ወንዶች መፀዳጃ ቤት ይዟት በመግባት ደፍሯታል ተብሏል።
ተጠርጣሪው ወንጀሉ ከተፈፀመበት ቦታ ተይዞ በአስገድዶ መድፈር እና አደንዛዥ ዕፅ ይዞ በመገኘት ተከሷል።
ደቡብ አፍሪቃ በአስገድዶ መድፈር ወንጀል በከፍተኛ ሁኔታ ከሚከሰትባቸው ሃገራት መካከል ትመደባለች።
የሃገሪቱ ፖሊስ ከመጋቢት በፊት በነበሩ 12 ወራት ብቻ ከ40 ሺህ በላይ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎችን መመዝገቡን አስታውቋል።
ይህ ማለት በቀን ከ110 በላይ የአስገድዶ መድፈር አደጋዎች በደቡብ አፍሪቃ ይከሰታሉ ሲል 'አፍሪቃ ቼክ' የተሰኘ መሥሪያ ቤት ያትታል።
በርከታ ደቡብ አፍሪቃውያን የታዳጊዋን ተገዶ መደፈር ተከትሎ ልጆቻችን አደጋ ላይ ናቸው ሲሉ ቁጣቸውን እየገለፁ ነው።
ዕለተ ቅዳሜ ፕሪቶሪያ በተሰኘችው የሃገሪቱ ከተማ በሚገኝ አንድ መመገቢያ ሥፍራ የተከሰተው ይህ ድርጊት ጉዳዩ ወዴት እየሄደ ነው በሚል ብዙዎች እንዲጠይቁ አስገድዷል።
የቢቢሲው ፑምዛ ፊህላኒነ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ዘወትር ማለዳ ከሚሰሙ ዜናዎች መካከል አስገድዶ መድፈር አንዱ ነው ሲል ሁኔታውን ያስረዳል።
ከታዳጊዋ መደፈር ሌላ ዶክተር ነኝ በማለት የ17 ዓመቷን አራስ የደፈረው ግለሰብ ሌላኛው መነጋገሪያ ሆኗል።
ቁጥራቸው እጅግ የላቀ ደቡብ አፍሪካውያን ፌስቡክና ትዊተር ወደመሳሰሉ ማህበራዊ ድር አምባዎች በመዝለቅ ሃዘናቸውንና ስጋታቸውን እየገለፁ ይገኛሉ።












