ሰብዓዊ መብት፡ ፓኪስታናዊቷ የመብት ተሟጋች በካናዳ ሕይወቷ አልፎ መገኘቱ ተሰማ

ፓኪስታናዊቷ የመብት ተሟጋች ካሪማ ባሎች በካናዳ ቶሮንቶ ሕይወቷ አልፎ መገኘቱ ተሰማ።
ይህንንም ተከትሎ የመብት ተሟጋች ቡድኖች በአሟሟቷ ላይ ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
በምዕራብ ፓኪስታን ባሎቺስታን ግዛት ቅስቀሳ በማድረግ የምትታወቀው የ37 ዓመቷ ካሪማ፤ የፓኪስታን ጦርን እና መንግሥትን በመተቸት ትታወቃለች።
ከአራት ዓመታት በፊትም በቢቢሲ 100 አነቃቂ ግለሰቦች ዝርዝር ውስጥ ተካትታ ነበር።
የቶሮንቶ ፖሊስ እሁድ ዕለት ግለሰቧ መጥፋቷን አስታውቆ ነበር።
የከተማዋ ፖሊስ ሰኞ ዕለት በትዊተር ገጹ ባሰፈረው ጽሁፍ የመብት ተሟጋቿ ለመጨረሻ ጊዜ የታየችው በከተማዋ ምዕራብ ክፍል ቤይ መንገድ ላይ እሁድ ዕለት መሆኑን ጠቅሷል።
ከዚያም በድጋሜ በትዊተር ሰሌዳው ላይ ባሰፈረው ጽሁፍ ዝርዝር ሁኔታዎችን ሳይገልፅ ካሪማ 'መገኘቷን' ጽፏል።
ይሁን እንጂ ጓደኞቿ እና አብረዋት የሚሰሩ የመብት ተሟጋቾች፤ ከዚያ በኋላ አስክሬኗ መገኘቱን ገልፀው፤ የሞቷ ምክንያት ግን ወዲያውኑ ግልፅ አለመደረጉን ተናግረዋል።
የካሪማ እህት፣ ማህጋንጂ ባሎች ማክሰኞ ዕለት የእህቷ ሞት "ለቤተሰቡ ብቻ ሳይሆን ለካሪማ ብሔራዊ እንቅስቃሴ አሳዛኝ ነው" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
አክላም "ካሪማ ወደ ካናዳ የሄደችው ስለፈለገች ሳይሆን በፓኪስታን ግልፅ በሆነ መንገድ ስለ መብት መሟገት የሚቻል ስላልነበረ ነው" ብላለች።
የባሎችስታን ግዛት ለረዥም ጊዜ የዘለቀ የተገንጣዮችን እንቅስቃሴ አስተናግዳለች።
ካሪማም በፓኪስታን እንቅስቃሴ እንዳያደርግ የተከለከለው የመብት ተሟጋች ቡድን፤ 'የባሎች ተማሪዎች ድርጅት' የቀድሞ ኃላፊ ነበረች። በቡድኑ ውስጥም የመጀመሪያዋ ሴት መሪ ሆና አገልግላለች።
ተቃውሞ ለማሰማት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አደባባይ የወጣችውም በአውሮፓዊያኑ 2005 መጀመሪያ አካባቢ ሲሆን ቦታውም ባሎቺስታን ቱርባት ነበር። ለተቃውሞ የወጣችውም ከጠፉት ዘመዶቿ የአንዱን ፎቶግራፍ ይዛ ነበር።
ካሪማ ከአገሯ የተሰደደችው በዚህ እንቅስቃሴዋ በሽብር ከተከሰሰች በኋላ ነው።
በአውሮፓዊያኑ 2015 ሕይወቷ አደጋ ላይ መሆኑን በመግለጽ ጥገኝነት ጠይቃ በካናዳ ኑሮዋን አድርጋ ነበር።
ወደ ቶሮንቶ ከገባች በኋላም አብሯት የሚሰራውን የመብት ተሟጋች ሃማል ባሎች ጋር ትዳር መስርታ፤ እዚያም በማህበራዊ ሚዲያዎች እና በካናዳና በአውሮፓ በሚካሄዱ የሰብዓዊ መብት እንቅስቃሴዎች ላይ በንቁ ስትሳተፍ ቆይታለች።
በባሎቺስታን ያሉ የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት በቅርብ ዓመታት ውስጥ ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች የደረሱበት አልታወቀም።
ይሁን እንጅ የፓኪስታን ጦር የክልሉን ራስ ገዝ አስተዳደር እየጨቆነ ነው በሚል የቀረበውን ክስ ተቃውሟል።
የካሪማን ሞት ተከትሎም የባሎቺስታን ብሔራዊ እንቅስቃሴ የ40 ቀናት የሐዘን ቀን አውጇል።
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል የደቡብ እስያ ቢሮ በትዊተር ገጹ ላይ
"የካሪማ ሞት በጣም አስደንጋጭ ነው፤ በአፋጣኝና በሚገባ ምርመራ መካሄድ አለበት፤ ወንጀለኞችም በሕግ ፊት መቅረብ አለባቸው" ብሏል።












