እስራኤል ወደ ሞሮኮ ‘ታሪካዊ’ የተባለ ቀጥታ የንግድ በረራ ጀመረች

የሞሮኮው ንጉሥ መሐመድ ስድስተኛ እና የእስራኤሉ ጠቅላእ ሚኒስትር ቤንዣሚን ኔተንያሁ

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES / EPA

የእስራኤል አውሮፕላን በእስራኤልና በሞሮኮ መካከል የተደረገውን የመጀመሪያ ቀጥታ የንግድ በረራ አደረገ።

ይህ የሆነው ሁለቱ አገራት በቅርቡ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማሳደግ ከተስማሙ በኋላ ነው።

አውሮፕላኑ በአረብኛ፣ በዕብራይስጥ እና በእንግሊዝኛ 'ሰላም' በሚል ቃል ያሸበረቀ ሲሆን ስለ ዲፕሎማሲያዊው ስምምነት ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር የሚሄዱ ከፍተኛ የእስራኤል ልዑካንን አሳፍሯል።

ሁለቱ አገራት ስምምነት ላይ የደረሱበት ድርድር የተካሄደው በዋሽንግተን ሲሆን የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አማች እና የመካከለኛው ምሥራቅ መልዕክተኛ ጄራረድ ኩሽነር ከእስራኤል ከተላከ ቡድን ጋር በመሆን ነበር።

ስምምነቱ የአረብ አገራት ከእስራኤል ጋር ያላቸውን ግንኙነት መደበኛ ለማድረግ ሲያካሂዷቸው የነበሩ ተከታታይ ስምምነቶች አካል ነው።

ሞሮኮ ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመጀመር ከተስማሙ የአረብ አገራት ዝርዝር ውስጥ መካተቷ የሚታወስ ነው።

ሞሮኮ ከነሐሴ ወር ወዲህ ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማሻሻል ከስምምነት የደረሰች አራተኛዋ አገር ናት።

ሞሮኮ ከእስራኤል ጋር ከስምምነት መድረሷን ተከትሎ በምዕራብ ሳሃራ ግዛት ለምታነሳው የይገባኛል ጥያቄ አሜሪካ እውቅና ለመስጠት መስማማቷ ይታወሳል።

በአልጄሪያ የሚደገፉ ፖሊሳሪዮ ግንባር በምዕራብ ሰሃራ የራስ ገዝ አስተዳደር ለመመስረት ከሞሮኮ ጋር ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ አለመግባባት ውስጥ ነበሩ።

በቅርቡ የትራምፕ አስተዳደር ሱዳን፣ ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ እና ባህሬን ከእስራኤል ጋር ሰላም እንዲያወርዱ ያደራደረ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም ከእስራኤል ጋር የሰላም ስምምነት የፈረሙት ግብጽ እና ዮርዳኖስ ሲደመሩ፤ ከአረብ ሊግ አባል አገራት ከእስራኤል ጋር የሰላም ስምምነት የደረሱት አገራት ቁጥር ወደ ስድስት ከፍ ይላል።

ዋይት ሃውስ ሞሮኮ ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደምትጀምር፣ ኢኮኖሚያዊ እና ባህላዊ ትብብሮችን ለመጀመር መስማማቷን በወቅቱ አስታውቆ ነበር።

በራባት እና ቴል አቪዝ የላይዘን ቢሮዎች በፍጥነት ሥራ ለማስጀምር፤ ከዚያም ኤምባሲዎች ለመክፈት ተስማምተዋል ተብሏል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በቴሌቪዥን በተላለፈው ንግግራቸው ስምምነቱን "ታሪካዊ" ያሉት ሲሆን፤ ለሞሮኮ ንጉስ ሞሐመድ ስድስተኛ ምስጋናቸውን አቅርበው ነበር።

ሞሮኮም ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመጀመር መስማማቷን የንጉሡ ቤተ-መንግሥት አረጋግጧል።

ግብጽ፣ ዩኤኢ እና ባህሬን፤ ሁለቱ አገራት የደረሱትን ስምምነት በደስታ ተቀብለነዋል ብለዋል።

የፍልስጤም መሪዎች ግን ስምምነቱን አጥላልተውት ነበር።

ፍልስጤማውያን የአረብ ሊግ አባላት ከእስራኤል ጋር የሰላም ስምምነት ማድረጋቸውን ሲቃወሙ ቆይተዋል።

የፍልስጤም መሪዎች እስራኤል ከአረብ አገራት ጋር ዲፕሊማሲያዊ ግንኙነት እንድትጀምር መፈቀዱ መብታችንን እንድትጋፋ የሚያበረታታ ነው ማለታቸው ይታወሳል።