ኮሮናቫይረስ ፡ በአዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ምክንያት አገራት ጥብቅ እርምጃ እየወሰዱ ነው

የፎቶው ባለመብት, EPA
በዩናይትድ ኪንግደም የተገኘው አዲሱ የኮሮናቫይረስ አይነት መላው ዓለምን አስግቷል።
አገራት ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የሚደረግ በረራን አግደዋል። በዚህም ከ40 በላይ አገራት ከዩናይትድ ኪንግደም ወደ አገራቸው የሚደረጉ በረራዎችን አግደዋል።
የአውሮፓ ሕብረት አባል አገራትም በዚህ ዙሪያ የጋራ ፖሊሲ ለማውጣት እየተወያዩ ነው።
ዴንማርክ ውስጥ አዲሱ የቫይረስ ዝርያ በመታየቱ ስዊድን ወደ ዴንማርክ የሚደረግ ጉዞ አግዳለች።
ዝርያው በከፍተኛ ሁኔታ የሚሰራጭ ነው። በከፍተኛ ደረጃ ጎጂ ስለመሆኑ ግን እስካሁን የተገኘ መረጃ የለም።
የዓለም ጤና ድርጅቱ ማይክ ራየን እንደሚሉት፤ አዲሱ የቫይረስ ዝርያ በወረርሽኙ ዝግመተ ለውጥ ሂደት የሚጠበቅ ነው።
የዩናይትድ ኪንግደም የጤና ሚንስትር ጸሐፊ ማት ሀንኮክ ከሰጡት ማብራሪያ በተቃራኒው አዲሱ ዝርያ "ከቁጥጥር አልወጣም" ብለዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም ከተገኘው የቫይረስ ዝርያ የተለየ አዲስ ዝርያ በደቡብ አፍሪካም ተገኝቷል። የደቡብ አፍሪካ ተጓዦች ላይ እገዳ እየተጣለም ነው።
አውሮፓ ውስጥ የተከሰተው ምንድነው?
አዲሱን የቫይረስ ዝርያ ስርጭት ለመግታት ብዙ የአውሮፓ አገሮች ወደ ዩናይትድ ኪንግደም በረራ አቋርጠዋል።
ፈረንሳይ ተጓዦች ላይ ክልከላ መጣሏን ተከትሎ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚንስትር ከፈረንሳዩ ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ንግድ ስለሚቀጥልበት መንገድ እንደሚነጋገሩ አስታውቀዋል።
ፈረንሳይ ተጓዦች ላይና የጭነት መኪና ላይም እገዳ ጥላለች። የንግድ ሚንስትሩ ክሌመንት ባውኔ ቀጣዩን እርምጃቸውን እንሚያሳውቁ ተናግረዋል።
ብራስልስ ውስጥ 27ቱ የአውሮፓ ሕብረት አባል አገሮች እየመከሩ ሲሆን፤ የጋራ ስምምነት ላይ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ቫይረሱ በተቀረው ዓለም
ሕንድ፣ ኢራን፣ ካናዳና ሌሎችም አገሮች ዩናይትድ ኪንግደም ላይ የበረራ እግድ ጥለዋል።
አሜሪካም በረራ ታቆማለች ተብሎ ይጠበቃል።
ሳዑዲ አረቢያ፣ ኩዌት እና ኦማን ድንበራቸውን ለዓለም አቀፍ ተጓዦች ዝግ አድርገዋል።
እስካሁን የአዲሱ ቫይረስ ዝርያ በዴንማርክ፣ አውስትራሊያ፣ ጣልያን እና ኔዘርላንድስ ተገኝቷል።
አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ የቫይረሱ ዝርያ ከተገኘባቸው ቦታዎች ውጪም ተሰራጭቶ ሊሆን ይችላል።
ዩናይትድ ኪንግደም የዘረ መል ቅንጣት ላይ ጥናት በማድረጓ አዲሱን የቫይረስ ዝርያ እንደደረሰችበትም አስረድተዋል።
በቤልጄም የሚሠሩት የቫይረስ አጥኚ ማርክ ቫን፤ "በቀጣይ ቀናት አዲሱ የቫይረሱ ዝርያ በብዙ አገሮች ይገኛል ብለን እንጠብቃለን" ብለዋል።
















