ኮሮናቫይረስ፡ 'አዲስ አይነት የኮሮናቫይረስ ዝርያ' በእንግሊዝ መገኘቱ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከዚህ ቀደም ከነበረው የተለየ ዝርያ ያለው አዲስ የኮሮናቫይረስ በአንዳንድ የእንግሊዝ አካባቢዎች በፍጥነት እየተዛመተ መሆኑ ተነገረ።
የዩናትድ ኪንግደም ጤና ሚንስትር ማት ሃንኮክ ለአገሪቱ ምክር ቤት አባላት እንደተናጉት፤ አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ቢያንስ በተለያዩ 60 ስፍራዎች መገኘቱ ተመዝግቧል ብለዋል።
ማት ሃንኮክ መንግሥታቸው ጉዳዩን ለዓለም ጤና ድርጅት ማሳወቁን እና የዩኬ ተመራማሪዎች በአዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ላይ ምርምር እያደረጉ መሆኑን አስታውቀዋል።
የጤና ሚንስትሩ እስካሁን ያሉት መረጃዎች ይህ ዝርያ ከዚህ ቀደም ከነበረው የኮሮናቫይረስ ዝርያ በላይ አደገኛ ስለመሆኑ አልያም የበለጸጉት የኮሮናቫይረስ ክትባቶችን ስለመቋቋሙ አያመለክቱም ብለዋል።
"በተለይ በደቡብ እንግሊዝ በርካታ በዚህ አዲስ የኮሮናቫይረስ ዝርያ የተጠቁ ከ1 ሺህ በላይ ሰዎችን አግኝተናል" ያሉት ማት ሃንኮክ፤ ክትባቶችን ለዜጎች በፍጥነት በማድረስ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።
የጤና ባለሙያው ፕሮፌሰር ክሪስ ዊቲ አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ በተለመደው የኮሮናቫይረስ ምርመራ እንደሚለይ ተናግረዋል። ፕሮፌሰሩ ጨምረውም በደቡብ እንግሊዝ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ በአዲሱ ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን አረጋግጠዋል።
በአዲሱ የኮሮናቫይረስ ውስጥ የቫይረሱ የፕሮቲን ብዛት እንደጨመረ የታወቀ ሲሆን፤ የቫይረሱ የፕሮቲን መጠን መጨመር በቫይረሱ ባህሪ ላይ የሚኖረው ለውጥ ምን ሊሆን እንደሚችል ግን ገና ግልጽ አይደለም።
በበርሚንግሃም ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር አለን ማክናሊ፤ "ብዙ መደናገጥ ያለብን አይመስለኝም። ይህ ማለት ቫይረሱ በፍጥነት የተላለፋል ማለት አይደለም ወይም አደገኛ ነው ማለት አይደለም" ብለዋል።
በቅርብ ቀናት ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ ፋይዘርና በባዮንቴክ የበለጸገውን የኮሮናቫይረስ ክትባት ለዜጎቻቸው መስጠት መጀመራቸው ይታወሳል።
95 በመቶ የኮሮናቫይረስን ይከላከላል የተባለለት ይህንን ክትባት ለዜጎች በመስጠት ዩናይትድ ኪንግደም ቀዳሚዋ አገር ሆና ነበር።















