ኮሮናቫይረስ፡ ስንት የኮቪድ-19 ክትባቶች አሉ? ለኢትዮጵያስ የትኛው ይደርሳታል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኮሮናቫይረስ ተከስቶ የዓለምን አጠቃላይ ገጽታ መቀየር ከጀመረ እንሆ አንድ ዓመት ሊሞላው ተቃርቧል። በዚህ ጊዜም ከ71 ሚሊዮን በላይ የምድራችን ነዋሪ በበሽታው መያዙ የተረጋገጠ ሲሆን ከ1.6 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በወረርሽኙ ሰበብ ህይወታቸውን አጥተዋል።
በሽታው ያላዳረሰው የዓለም ክፍል የሌለ ሲሆን እንደተሰጋው የከፋ ጉዳትን ባያደርስም በአፍሪካ አገራት ውስጥም ከ2.3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በበሽታው ሲያዙ ከ56 ሺህ በላይ ድግሞ ለሞት ተዳርገዋል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ በኢትዮጵያ ከ116 ሺህ ሰዎች በላይ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን ከ1 ሺህ 880 በላይ ሰዎች ህይወታቸው አልፏል።
ከዓለም ዙሪያ የተሰባሰቡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በበሽታው መያዛቸው ከተረጋገጡ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ከበሽታው ያገገሙ ቢሆንም አስካሁን ፈዋሽነቱ የተረጋገጠ መድኃኒት ለቫይረሱ አልተገኘም።
በሽታው ቻይና ውስጥ መከሰቱ ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ አገራት ለበሽታው መከላከያ የሚሆን ክትባት እንዲሁም የተያዙ ሰዎችን ለማከም የሚያገለግል መድኃኒት ለማግኘት ሊቃውንት ቀን ከሌት እየጣሩ ይገኛሉ።
እስካሁን በተደረጉ ምርምሮችና ሙከራዎች በርካታ ተስፋ ሰጪ የክትባት ውጤቶች መገኘታቸው ከመነገሩ ባሻገር፤ በሽታውን ለመከላከል ያስችላሉ የተባሉ ጥቂት ክትባቶችም ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ለበሽታው ተጋላጭ ናቸው ለተባሉ ሰዎች መሰጠት ተጀምሯል።
በዚህ ረገድ ቀዳሚውን የተጠቃሚነት ዕድል ያገኙት ባለጸጋ አገራት ሲሆኑ የዓለም ጤና ድርጅት ደግሞ ክትባቶቹ ለሁሉም እንዲዳረስ ጥረት እያደረገ መሆኑን አመልክቷል። አገራትም ለዜጎቻቸው ክትባቱን ለማቅረብ ባላቸው አማራጮች ሁሉ እየሞከሩ ነው።
ኢትዮጵያም እንዲሁ ኮቫክስ ከተሰኘው ዓለም አቀፍ የክትባት ድጋፍ ሰጪና እቅራቢ በኩል ለአገልግሎት ከሚቀርቡት የኮሮናቫይረስ ክትባት ለማግኘት ጥያቄ እንዳቀረበች የጤና ጥበቃ ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ባለፈው ሳምንት ገልጸዋል።
ሚኒስትሯ ጨምረውም ለአገልግሎት ብቁ ከሆኑ የክትባት አይነቶች መካከል ኢትዮጵያም እንድታገኝ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረው፤ በኮቫክስ በኩል ክትባቱን በፍጥነት ለማግኘትና በቅድሚያ መከተብ ለሚገባቸው ወገኖች እንዲደርስ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

ለመሆኑ የትኞቹ ክትባቶች ጥቅም ላይ ውለዋል?
በአሁኑ ጊዜ በርካታ መድኃኒት አምራች ኩባንያዎችና አገራት ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የሚሆን ክትባት በማበልጸግ ላይ ሲሆኑ ጥቂቶቹም በስራ ላይ መዋል ጀምረዋል።
ፋይዘር/ባዮንቴክ
ኮሮናቫይረስን በመከላከል 90 በመቶ ውጤታማ ነው የተባለው ይህ የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ይፋ የሆነው በፈረንጆቹ ሕዳር 9/2020 ላይ ነበር።
በወቅቱ ክትባቱን ይፋ ያደረጉት ፋይዘር እና ባዮኤንቴክ ኩባንያዎች ግኝቱ ለሳይንስና ለሰው ልጅ ትልቅ እድል ነው ብለዋል።
የአሜሪካ እና የጀርመን ኩባንያ የሆኑት ፋይዘር እና ባዮንቴክ በስድስት የተለያዩ ሃገራት 43 ሺህ 500 ሰዎች ላይ መሞከራቸውን የገለፁ ሲሆን አንድም ጊዜ አሳሳቢ የጤና ችግር አልታየም ብለዋል።
ፋይዘርና ባዮንቴክ ክትባቱን በፈረንጆቹ የህዳር ወር መጨረሻ ጥቅም ላይ ለማዋል ጥያቄ ማቅረባቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ይህን ተከትሎም ዩናይትድ ኪንግደም ክትባቱ ጥቅም ላይ እንዲውል በመፍቀድ ከዓለማችን ቀዳሚዋ አገር ሆናለች።
ዩናይትድ ኪንግደም ለመጀመሪያ ጊዜ የኮሮናቫይረስ ክትባትን ማክሰኞ ዕለት ለዜጎቿ መስጠት የጀመረች ሲሆን የዘጠና ዓመቷ አዛውንት የፋይዘር/ባዮንቴክ ክትባትን በመውሰድ በዓለም የመጀመሪያዋ ሰው ሆነዋል።
በመላው ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የሚገኙ ከ70 በላይ የሚሆኑ ሆስፒታሎች እድሜያቸው ከ80 ዓመት በላይ ለሆኑ አዛውንቶች እና ለጤና ባለሙያዎች ክትባቱን ለመስጠት መዘጋጀታቸው ተገልጿል።
የአሜሪካ የምግብና መድኃኒት አስተዳደር መስሪያ ቤትን (ኤፍዲኤ) የሚያማክሩ ባለሙያዎች በፋይዘር/ባዮንቴክ የበለጸገው የኮሮናቫይረስ ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል ሀሳብ ማቅረባቸውም ተገልጿል።
ባለሙያዎቹ ይህን ምክረ ሃሳብ የሰጡት 23 አባላት ያሉት የባለሙያዎች ቡድን ክትባቱ ሊፈጥረው የሚችለው ስጋት ከሚሰጠው ጥቅም አንጻር ምን ሊመስል እንደሚችል ምክክር ካደረጉ በኋላ ነው ተብሏል።
የአሜሪካ የጤና ሚንስትር አሌክስ ረቡዕ ዕለት ''በሚቀጥሉት ቀናት ክትባቱ በእጃችን ሊገባ ይችላል፤ በሚቀጥለው ሳምንት ደግሞ እጅግ ተጋላጭ የሆኑትን ዜጎች መከተብ ልንጀምር እንችላል'' ብለዋል።
የፋይዘር/ባዮንቴክ ክትባት እስካሁን በዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ፣ ባህሬን እና ሳኡዲ አረቢያ ጥቅም ላይ ለመዋል ፍቃድ አግኝቷል።


ሞደርና
የዩናይትድ ስቴትስ መድኃኒት አምራች ኩባንያ የሆነው 'ሞደርና' ከኮሮናቫይረስ 95 በመቶ የሚከላከል አዲስ ክትባት ማግኘቱን ይፋ ካደረገ ሰነባብቷል። በአሁኑ ሰአትም ከአውሮፓና አሜሪካ ፈቃድ ሰጪዎች ክትባቱን ለመጠቀም የሚያስችል ፈቃድ ጠይቆ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።
ሞደርና የምርምር ውጤቱን ይፋ ያደረገበትን ዕለት 'ታላቅ ቀን' በማለት ሐሴቱን የገለፀ ሲሆን፤ በቅርብ ሳምንታትም ክትባቱን ለመጠቀም ፈቃድ እንደሚያገኝ አስታውቋል።
የቤተ ሙከራ ሂደቶች እንደሚያሳዩት ኤምአርኤንኤ የተሰኘው ክትባት 94 በመቶ ውጤታማና ሰዎችን ከኮሮናቫይረስ የሚያድን ነው።
የክትባቱ ሙከራ አሜሪካ ውስጥ ያሉ 30 ሺህ ሰዎችን ያሳተፈ ሲሆን፤ ግማሾቹ በየአራት ሳምንቱ ክትባቱ ሲሰጣቸው ግማሾቹ ደግሞ ጥቅምና ጉዳት የሌለው መርፌ ተወግተው ውጤቱን ለመለየት ተሞክሯል።
ከዚህ ሙከራ በተገኘ ውጤት መሠረት 94.5 በመቶ ሰዎች በክትባቱ ምክንያት ለኮሮናቫይረስ ሳይጋለጡ ቀርተዋል ተብሏል።
ስለ ክትባቱ ውጤቱ የቀረበው ዘገባ ጨምሮም፤ ሙከራ ከተደረገባቸው መካከል 11 በኮቪድ-19 ክፉኛ የታመሙ ሰዎች የመከላከል አቅም አዳብረዋል ይላል።

ስፑትኒክ 5
ይህ ሩሲያ ሰራሽ ክትባት ይፋ በተደረገ ጊዜ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በአገር ውስጥ በተደረገ ምርምር አገር በቀል ክትባት አግኝተናል፤ ለሰዎች አገልግሎት እንዲውልም ይፋዊና ብሔራዊ ፍቃድ ሰጥተናል ብለው ነበር።
በዓለም የመጀመርያው የተባለው ይህ ስፑትኒክ-5 ክትባት ሞስኮ የሚገኘው ጋማሊያ ኢንስቲትዩት ነው ያመረተው። ክትባቱ ይፋ የተደረገውም ነሀሴ ወር ላይ ነበር።
ኢንስቲትዩቱ እንደሚለው ክትባቱ አስተማማኝ የመከላከል አቅም ይሰጣል።
ፑቲን በበኩላቸው ገና ቀደም ብሎ "ይህ ክትባት አስተማማኝ እንደነበር አውቅ ነበር" ብለዋል። "ሁሉንም ሳይንሳዊ ሂደቶችን በአስተማማኝ ሁኔታ ማለፍ ችሏል" ሲሉም አስረግጠው ተናግረዋል።
ፑቲን ከልጆቻቸው ለአንዷ ክትባቱ ተሰጥቷት ትንሽ አተኮሳት እንጂ ምንም አልሆነችም ብለዋል። ፑቲን የትኛዋ ልጃቸው ክትባቱን ወስዳ እንዳተኮሳት ግን በስም አልገለጹም።
የሩሲያ ሳይንቲስቶች የመጀመሪያ ዙር ሙከራዎች ተደርገው ሁሉም ድንቅ ውጤት አስመዝግበዋል ብለዋል።
ሳንቲስቶቹ ሰዎች ላይ ጉንፋንን የሚያመጣው አዲኖቫይረስ የተሰኘውን የተላመደ የተህዋስ ቅንጣት ተጠቅመው ነው ክትባት ሰራን ያሉት።
ይህን ለማዳ ተህዋሲ አዳክመው ወደ ሰውነት በማስገባት ሕዋስ በማቀበል ክትባቱ ሰውነት ኮቪድ-19 ተህዋሲ ሲገባ ነቅቶ እንዲዋጋ ያደርገዋል ብለዋል።
በአውሮፓውያኑ ታሕሳስ 5/2020 ላይ ደግሞ ይሄው ክትባት በሩሲያዋ መዲና ሞስኮ መሰጠት ተጀምሯል።
በመጀመሪያው ዙር ክትባቱን ለመውሰድ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተመዝግበዋል።
ሩሲያ ምን ያህል ክትባት ማምረት እንደምትችል ግልጽ ባይሆንም፤ አምራቾች እስከ ዓመቱ መገባደጃ ሁለት ሚሊዮን ጠብታ እንዲያዘጋጁ ይጠበቃል።
13 ሚሊዮን ሰዎች የሚኖሩባት የሞስኮ ከተማ ከንቲባ ሰርጌ ሶቢያን እንዳሉት፤ ክትባቱ ለማኅበረሰብ አገልግሎት ሰጪዎች፣ ለጤና ባለሙያዎች እና ለትምህርት ቤት ሠራተኞች ይሰጣል።
ተጨማሪ ክትባቶች ሲመረቱ ለተቀረው ማኅበረሰብ እንደሚዳረስ ከንቲባው ጠቁመዋል።
ከላይ በተዘረዘሩት የሙያ መስኮች የተሰማሩና እድሜያቸው ከ18 እስከ 60 የሆኑ ዜጎች በድረ ገጽ ተመዝግበዋል። በሞስኮ ከጠዋቱ 2 ሰዓት እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት የክትባቱን አገልግሎት የሚሠጡ 70 ማዕከሎች ተከፍተዋል።
ክትባቱ የተሰጣቸው ባለፉት 30 ቀናት የመተንፈሻ አካል ህመም የገጠማቸው፣ የከፋ የጤና እክል ያለባቸው፣ ነፍሰ ጡር እና የሚያጠቡ እናቶች እንደሚለዩ ተገልጿል።

ሲኖቫክ
መላው ዓለም ለኮሮናቫይረስ ክትባት ለማግኘት ደፋ ቀና ሲል ቻይናም እጇን አጣጥፋ አልተቀመጠችም። ሲኖቫክ የተባለ ክትባት መስራት ከጀመረች ሰነባብታለች። እንደውም በጎ ፈቃደⶉችን መከተብ ከጀመረች ቆየት ብላለች።
በቻይና በሙከራ ላይ የሚገኘው የኮቪድ-19 ክትባት አመርቂ የሚባል ውጤት እያስገኘ ነውም ተብሏል። ሆኖም ክትባቱ አመርቂ ውጤት ያስገኘው በረዥም የሙከራ ሂደት ውስጥ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ሳይሆን፣ መካከለኛ ምዕራፍ በሚባለው ክፍል ነው።
ተመራማሪዎች እንዳረጋገጡት ከቻይና ሰራሽ ክትባቶች አንዱና ታዋቂ እየሆነ የመጣው በሲኖቫክ ባዮቴክ የተመረተው ሲኖቫክ ክትባት በ700 ሰዎች ላይ ተሞክሮ ይበል የሚያሰኝ ውጤት አስገኝቷል።
ክትባቱ የተሞከረባቸው ሰዎች በሽታን የመከላከያ ህዋሳቸውን አንቅቶ ቫይረሱን መመከት እንደቻለ ተደርሶበታል።
ላንሴት በሚባለው ሥመ ጥር የሳይንስ ጆርናል ላይ ይህንን ክትባት በተመለከተ የተዘገበው፤ ክትባቱ ለጊዜው በምዕራፍ አንድና ሁለት ያስመዘገበው ውጤት እንጂ አሁን ያለበትን ደረጃ አይገልጽም።
በተጨማሪም የስኬት ምጣኔው ምን ያህል እንደሆነ ይፋ አልተደረገም።
በዚህ ጆርናል ላይ ስለዚህ ቻይና ሰራሹ ክትባት ከጻፉት ተመራማሪዎች አንዱ የሆኑት ዙ ፋንቻይ እንደሚሉት፤ በምዕራፍ አንድ እና በምዕራፍ 2 ሙከራዎች 600 ሰዎች ላይ ጥናት ተደርጎ ክትባቱ ለአስቸኳይ ሕክምና አገልግሎት ላይ መዋል ይችላል የሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሷል።
ነገር ግን ወሳኝ በሚባው በምዕራፍ ሦስት ሙከራ ላይ ይህ የቻይና ክትባት ስላስገኘው ውጤት በተጨባጭ ተአማኒ ሳይንሳዊ ጆርናል ላይ የተጻፈ ዘገባ የለም።
በቻይና በአሁን ሰዓት ሙሉ በሙሉ ሊባል በተቃረበ ደረጃ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በቁጥጥር ሥር የዋለበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ሆኖም ቻይና ለዜጎቿ ይህንን ክትባት መስጠቷን ቀጥላበታለች።
በአሁኑ ሰአት ደግሞ መቀመጫውን ቤዢንግ ያደረገው የክትባት አምራቹ ኩባንያ ያዘዛቸው በርካታ የህክምና ቁሳቁሶች ከኢንዶኔዢያ መግባት ጀምረዋል። ይህ ደግሞ አገሪቱ በቅርቡ ዜጎቿን በይፋ መከተብ ልትጀምር እንደሆነ ማሳያ ነው ተብሏል።
በዓለም ላይ ኮቪድ-19 ከፍተኛ ጉዳት ካደረሰባቸው አገራት ተርታ የምትመደው የደቡብ አሜሪካዋ ትልቅ አገር ብራዚል በበኩሏ ቻይና ሰራሽ ክትባት ለሕዝቤ አድላለሁ ማለቷ የሚታወስ ነው።
የሳኦ ፖሎ ገዥ ጃዎ ዶሪያ እንዳሉት የፌዴራል መንግሥት 46 ሚሊዮን ጠብታዎችን ለመግዛት ስምምነት ላይ ደርሷል።
የክትባት ዘመቻው መቼ ይጀመራል በሚል የተጠየቁት የሳኦ ፖሎ ገዥ በፈረንጆች አዲሱ ዓመት የመጀመርያ ወር ላይ ሊሆን ይችላል ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አስትራዜኒካ እና ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ
አስትራዜኒካ እና ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ እያበለፀጉ ያሉት ክትባት ከፍተኛ ተስፋ ከተጣለባቸው ክትባቶች መካከል ነው።
ይሄው ክትባት በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በሙከራ መልክ ተሰጥቷል። ደቡብ አፍሪካ ለዚህ የክትባት ሙከራ የተመረጠችው በዘርፉ ባሏት ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆን ከአፍሪካ በርካታ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ያሉባትና ወረርሽኙም በፍጥነት እየተስፋፋባት በመሆኑ ነው።
ይህ የክትባት ሙከራ ኦኤክስ1ኮቪድ-19 ክትባት የሚባል ሲሆን፤ ኮሮናቫይረስን የሚያስከትለው ሳርስ-ኮቪ-2 በተባለው ቫይረስ ሰዎች እንዳይያዙ ለመከላከል የታለመ ነው።
በደቡብ አፍሪካ የሚደረገው የክትባት ሙከራ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ጥልቅ ፍተሻ ተደርጎበት በደቡብ አፍሪካ መንግሥት የጤና ምርቶች ተቆጣጣሪ ተቋምና በዊትስ ዩኒቨርስቲ ፈቃድ ተሰጥቶታል ተብሏል።
ይህ ክትባት ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ከአራት ሺህ ሰዎች በላይ የተሳተፉበት ክሊኒካል ሙከራ የተደረገበት ሲሆን፤ በደቡብ አፍሪካ ከሚደረገው ሙከራ ጋር ተመሳሳይና ተዛማጅ የሆነ ሙከራ ብራዚል ውስጥ ሊጀመር እንደሆነ ተገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም ከሁሉም የላቀ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የሚሳተፉበት የዚህ ክትባት ሙከራ አሜሪካ ውስጥ በ30 ሺህ ሰዎች ላይ ለማካሄድ ዕቅድ ተይዟል።
በሌሎች ድርጅቶች የሚሠሩ እና በሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ክትባቶች ሙከራ ተጨማሪ ውጤቶች በሚቀጥሉት ሳምንታት እና ወራቶች ይወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በአሁኑ ሰአትም የመጨረሻው የሙከራ ደረጃ ላይ የሚገኙ በርካታ ተጨማሪ ክትባቶች አሉ። ከነዚህም መካከል ከታች የተዘረዘሩት የሚጠቀሱ ናቸው።
- ካንሳይኖ በቻይና ከሚገኘው የቤጂንግ የባዮቴክኖሎጂ ተቋም ጋር- ቻይና
- ጋማሊያ ምርምር ተቋም-ሩሲያ
- ጆንሰን
- ቤጂንግ የባዮሎጂካል ምርቶች ተቋም እና ሲኖፋርማ- ቻይና
- ሲኖቫክ እና ኢንስቲዩቶ ቡታንታን- ብራዚል
- የዉሃን የባዮሎጂካል ምርቶች ተቋም እና ሲኖፋርማ- ቻይና
- ኖቫቫክስ- አሜሪካ

የክትባቶቹ ደኅንነትስ?
ክትባቱ እስካሁን በደኅንነት ጉዳይ ይህ ነው የሚባል ነገር አልተነሳበትም። ነገር ግን የትኛውም መድኃኒት መቶ በመቶ እንከን አልባ ሊሆን አይችልም።
አንዳንድ ተሳታፊዎች ክትባቱን የወሰዱ ሰሞን መጠነኛ ድካም፣ ራስ ምታትና ሕመም እንደተሰማቸው አስታውቀዋል።
የሞደርና እና የፋይዘር ክትባት ከ90 በመቶ በላይ ውጤታማ መሆናቸው ተነግሯል።
ነገር ግን የሁለቱም ድርጅቶች ውጤት የመጨረሻ ደረጃ ላይ አልደረሰም። ውጤታማነቱም ሊቀየር ይችላል ተብሏል። ቢሆንም የሞደርና ክትባት ማቀዝቀዣ ውስጥ ለማስቀመጥ ከሌሎቹ ክትባቶች በተለየ ቀላል እንደሆነ ተነግሯል።
የሞደርና ክትባት ማቀዝቀዣ ውስጥ እስከ አንድ ወር መቆየት ሲችል የፋይዘር ግን ለአምስት ቀናት ብቻ ነው የሚቆየው።
ሩስያ የለቀቀችው ስፑትኒክ 5 የተሰኘው ክትባትም 92 በመቶ የመከላከል አቅም እንዳለው ተነግሯል።














