ዩኬ እና ሩስያ ክትባቶቻቸውን አጣምረው ሙከራ ሊያደርጉ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዩናይትድ ኪንግደም እና የሩስያ ሳይንቲስቶች የኮሮናቫይረስ ክትባቶቻቸውን አጣምረው ሙከራ ሊያደርጉ ነው።
የኦክስፎርድና አስትራዜኒካ ክትባት ከሩስያው ስፑትኒክ ጋር ቢጣመር ቫይረሱን በተሻለ ሁኔታ መከላከል ይቻል ይሆናል።
ሁለት ተመሳሳይ ክትባቶችን ማዋሀድ የሰዎችን በሽታ የመከላከል አቅም በከፍተኛ ሁኔታ ሊያሳድግ ይችላል።
ሙከራው የሚካሄደው ሩስያ ሲሆን፤ ከ18 ዓመት በላይ በሆኑ ሰዎች ላይ ነው የሚሞከረው።
ኦክስፎርድ የሠራው ጠብታ ሰዎች ላይ ተሞክሮ አስተማማኝ እና ውጤታማ መሆኑን በቅርቡ አስታውቋል።
ተመራማሪዎች ክትባቱ ለአረጋውያን እንደሚሠራ ለማረጋገጥ መረጃ እየሰበሰቡ ነው። ዩኬ ውስጥ ፍቃድ እስኪሰጣቸው እየጠበቁም ነው።
አስትራዜኒካ የተለያዩ የአድኖቫይረስ ክትባቶችን በማዋሀድ የተሻለ በሽታ የመከላከል አቅም ማዳበር ይችሉ እንደሆነ እየተመራመረ ነው።
ክትባቶችን ማደባለቅ ዘለግ ላለ ጊዜ ሰውነት በሽታን እንዲከላከል እና በቫይረሱ ሳይያዙ ረዥም ጊዜ ለመቆየት ይረዳከል የሚል ተስፋ አለ።
የኦክስፎርዱ እንዲሁም የሩስያው ስፑትኒክ ክትባትም ጉዳት አልባ ቫይረስን በመጠቀም ነው የተሠሩት። ይህም ሰውነት በሽታውን መቋቋም እንዲችል ያግዛል።
የኦክስፎርድ ክትባት መጀመሪያ ላይ ግማሽ ጠብታ ከዛም አንድ ሙሉ ጠብታ ይሰጣል። ይሄ ሂደት በአንድ ጊዜ ሁለት ጠብታ ከመስጠት የተለየ ነው።
የኦክስፎርድና አስትራዜኒካ ክትባት ከስፑትኒክ ጋር የሚመሳሰሉት ሁለቱም የሳርስ-ኮቭ-2 የዘረ መል መዋቅርን የያዙ በመሆናቸው ነው።
የነዚህ ክትባቶች አሠራር ከፋይዘር እና ባዩቴክ ክትባቶች የተለየ ነው። እነዚህ ሁለት ክትባቶች በዩኬ፣ ካናዳ፣ ባህሬን፣ ሳኡዲ አረቢያ ፍቃድ አግኝተዋል። የጤና ባለሙያዎች ክትባቶቹ በአሜሪካም ፍቃድ እንዲሰጣቸው መክረዋል።
የስፑትኒክ የመጨረሻ ሙከራ ደረጃ ላይ የተገኘው ቅድመ መረጃ ክትባቱ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ይጠቁማል።
ሩስያ የኮሮናቫይረስ ክትባትን በማስመዝገብ ከዓለም ቀዳሚ አገር ናት። አሁን ለዜጎች እየተሰጠም ይገኛል።












