ኮሮናቫይረስ፡ ዓለም 7 ቢሊዮን ዜጎቿን መከተብ ትችል ይሆን?

ክትባት

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

የምስሉ መግለጫ, ክትባት

በመላው ዓለም የሚገኙ ጥቂት የማይባሉ የተመራማሪዎች ቡድን በፍጥነት ለኮቪድ-19 የሚሆን ክትባት ለማግኘት ሌት ተቀን እየሰሩ ይገኛሉ።

በርካታ መሪዎችም ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ ተባብረን ይህንን ለኮሮናቫይረስ ክትባት ማግኘት አለብን የሚል መልዕክታቸውን እያስተላለፉ ነው።

ለመሆኑ ተመራማሪዎች ከሚሰሩት ክትባቶች ለ7 ቢሊየን ህዝብ በበቂ ሁኔታ ክትባቱን ማዳረስ ይቻል ይሆን?

በቅርቡ ደግሞ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ክትባት ስለማግኘታቸው አስታውቋል። በአገር ውስጥ በተደረገ ምርምር አገር በቀል ክትባት አግኝተናል፤ ለሰዎች ጥቅም አገልግሎት እንዲውልም ይፋዊና ብሔራዊ ፍቃድ ሰጥተናል ብለዋል።

አሁን ሳይንቲስቶችን እያነጋገረ ያለው ነጥብ የትኛውም መድኃኒት ወይም ክትባት ሲፈጠር ሦስት ጥብቅ ምዕራፎችን ማለፍ እያለበት ፑቲን በሁለት ምዕራፍ ብቻ መድኃኒቱ ተፈጠረ ማለታቸው ነው።

በዓለም የመጀመርያው የተባለው ይህ ስፑትኒክ-5 ክትባት ሞስኮ የሚገኘው ጋማሊያ ኢንስቲትዩት ነው ያመረተው። ኢንስቲትዩቱ እንደሚለው ክትባቱ አስተማማኝ የመከላከል አቅም ይሰጣል።

ሩሲያ ቀድማ ክትባቱን ስለማግኘቷ ትግለጽ እንጂ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚገኙ በርካታ ተመራማሪዎች ክትባቱን ለማግኘት ደፋ ቀና እያሉ ሲሆን በቅርብ ወራት ውስጥ አመርቂ ውጤት ይዘው እንደሚመጡ ይጠበቃል።

ከነዚህ መካከል አንዱ የሆነውና ኦክስፎርድሻየር የሚገኘው ሃርዌል የሳይንስ ካምፓስ ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል። ማዕከሉ በዩናይትድ ኪንግደም የክትባቱ ምርምርና ምርት ዋነኛ ማዕከል እንዲሆንም ተደርጓል።

''እጅግ በጣም ጠባብ በሆነ የጊዜ ገደብ ውስጥ ነው እየሰራን ያለነው፤ ከተለመደው አሰራር ከሚኖረን ጊዜ በግማሽ ባነሰ ምርምሩን ማስኬድ ይጠበቅብናል። በ2022 መጨረሻ አካባቢ ዝግጁ ሊሆን የሚገባውን ክትባት በ2021 ዝግጁ ለማድረግ እየሰራን ነው'' ብለዋል የማዕከሉ ዋና ስራ አስፈጻሚ ማቲው ዱካርስ።

ማቲው ዱካስ እንደሚሉት ዓመታዊ እረፍታቸውን እንኳን አልወሰዱም። ምክንያቱም ማዕከሉ በየትኛውም ጊዜ ለኮቪድ-19 የሚሆን ክትባት ሊያመርት ስለሚችል ነው። በየቀኑ ከቡድኑ አባላት ጋር ስለደረሱበት ሂደት መወያየት ግድ ነው።

''ከባድ ኃላፊነት ነው። እጅግ በጣም ወሳኝ ሰአት ላይ ነው ያለነው። በአንድ አገር የሚወሰን ችግር አይደለም፤ መላው ዓለም በዚሁ ወረርሽኝ ምክንያት ከባድ መከራ ውስጥ ገብቷል'' ሲሉ ያስረዳሉ።

''ልክ በቤት ውስጥ ኬክ እንደ መጋገር አይነት ስሜት አለው። ተጨንቀን ተጠበነን ለራሳችን ብለን የምንሰራውን ኬክ ለ7 ቢሊየን ሰዎች ማዘጋጀት እንደማለት ነው''

የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ዓለማቀፍ ሙከራ ማድረግ እንኳን ሳይጀመር ክትባቱን ለማምረት የሚያስችል ቤተ ሙከራ በጊዜያዊነት ለማዘጋጀት ተገዷል። ክትባቱ ሲገኝ ደግሞ የሰው ልጅ በርካታ አይነት ያላቸው ክትባቶችን ለቢሊየኖች በሚበቃ መልኩ ማዘጋጀት ይጠይቃል።

ማምረት ብቻ ሳይሆን ክትባቶቹ እንዳይበላሹ አድርጎ ማሸግ፣ ማጓጓዝ እና ለተጠቃሚዎች ማድረስ ቀላል የሚባል ተግባር አይደለም። በአራቱም የዓለማችን ማዕዘናት የሚገኙ ሰዎችን መድረስ መቻል በራሱ ወራትን ካልሆነም ዓመታት ሊፈጅ ይችላል።

ዓለማ አቀፉ የክትባት ጥምረት በቅጽል ስሙ 'ጋቪ' ይባለል። አገራት ክትባቱ ሲገኝ እንዴት ሊሰራጭ እንደሚችል ከአሁኑ ሊያስቡበት እንደሚገባ እያስጠነቀቀ ይገኛል።

ምንም እንኳን በዚህ ሰዓት በሙከራ ላይ ካሉ ክትባቶች መካከል የትኛው ቀድሞ ይደርሳል የሚለውን መገመት ቢከብድም፤ የበለፀጉት አገራት በመቶ ሚሊዮን ዶላሮች እያወጡ ከላብራቶሪዎች እነዚህን ክትባቶች እየገዙ ይገኛሉ።

ለምሳሌ ዩናይትድ ኪንግደም የክትባት ሙከራውን ከሚያቀርቡት አስትራዜንካ፣ ፋይዘርና ባዮንቴክና ቫልኔቫ ከተባሉት ኩባንያዎች ጋር ስምምነት ፈርማለች።

መንግሥታት ከሁሉ በፊት የራሳቸውን አገራት በማስቀደምም ላይ ይገኛሉ። እነዚህ አገራት በበላይነት ክትባቶቹን ከያዟቸው ቢሊዮኖችን ሊገለሉ እና ክትባቱ በፍጥነት ላይደርሳቸው ይችላል። በተለይም ተጋላጭ ለሆኑት ማኅበረሰብ አለመድረሱ ቀውስን የሚፈጥር ነው።