በሰርጋቸው ዕለት ለደረሰ ጥቃት ተጠያቂ የተደረጉት ጥንዶች

በሕይወታቸው በእጅጉ የሚደሰቱበት ቀን መሆን ነበረበት፤ ነገር ግን እጅግ ዘግናኙ ቀን ሆኖ አልፏል።
ሚርዋስ እና ሪሃና ባሳለፍነው ዓመት በአፍጋኒስታን ዋና ከተማ ካቡል ሰርጋቸውን በሚያካሂዱበት ስነ-ስርዓት ላይ አንድ የአይኤስ ታጣቂ ባደረሰው የቦምብ ጥቃት 90 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።
ጥንዶቹ በደረሰው ፍንዳት በርካታ የቤተሰብ አባሎቻቸውን፣ ጓደኛና ወዳጅ ያጡ ሲሆን በወቅቱ የደረሰባቸው የስነ አእምሮአዊ ጫናም ቀላል የሚባል አልነበረም።
በዚህ ሳምንት ደግሞ ጥቃቱ ከደረስ አንድ ዓመት ይሞላዋል። የ18 ዓመቷ ሪሃና በዛች ዕለት ምን እንደተፈጠረ በይፋ ለማውራት ለመጀመሪያ ጊዜ ፈቃደኛ ሆናለች።
''በየቀኑ ሌሊት ላይ ቅዠት ይቀሰቅሰኛል፤ ሁሌም ስለማለቅስ እንቅልፍ አይወስደኝም'' ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
እሷ እንደምትገልጸው በርከት ያሉ ሰዎች የተሰበሰቡቡት ቦታ ስትገኝ ጭንቀት የሚይዛት ሲሆን በመኪና መንቀሳቀስም በእጅጉ ትፈራለች።
''በማንኛውም አጋጣሚ ተኩስ ወይም የፍንዳታ ድምጽ ስሰማ በሰርጌ ዕለት የተፈጸመውን ነገር ያስታውሰኛል፤ ነገሮቹ ሁሉ በድጋሚ የሚፈጠሩ እየመሰለኝ በጣም እፈራለው" ብላለች።
ጥቃቱ ከተፈጸመ አንደኛ ዓመቱን ለማስታወስ ዘመዶቻቸውና ወዳጆቻቸው ሰርጉ ከተካሄደበት አዳራሽ ፊትለፊት በመሰብሰብ ቦምቡን ያፈነዳው አካል ለፍርድ እንዲቀርብ ድምጻቸውን አሰምተዋል። ሚርዋስ ግን በቦታው አልተገኘም ነበር።
ስለፍንዳተው ማሰብ በራሱ ሰውነቱን እንደሚያንቀጠቅጠው ይናገራል።
''ከፍንዳታው በፊት ሁላችን በደስታ ተውጠን ነበር። ነገር ግን በድንገት ሁላችን ከሰማይ ወደ ምድር የወደቅን አይነት ስሜት ተሰማኝ። በቅጽበት ውስጥ ደስታችን ወደ ሀዘንና ዋይታ ተቀየረች።''
የጥንዶቹ የሰርግ ስነ-ሰርዓት ላይ አይኤስ የተባለው አክራሪ እስላማዊ ቡድን ጥቃት የፈጸመው አፍጋኒስታን ውስጥ እንደ አናሳ ከሚቆጠሩት ሺአዎች አባል ስለሆኑ ነው። አይኤስም ሺአዎች እስልምናን ሙሉ በሙሉ አይቀበሉም በማለት ባለፉት ዓመታት ተደጋጋሚ ጥቃት ይፈጽማል።
ለሪሀና እና ሚርዋስ የሰርጋቸው ዕለት የደረሰው ጥቃት አልበቃ ብሎ አንደንድ ዘመዶችና ጓደኞች ለፈሰሰው ደም እናንተ ናችሁ ተጠያቂዎች በማለት ወንጅለዋለቸዋል።
''አንድ ቀን አስቤዛ ለመግዛት ስንቀሳቀስ አንዲት በሰርጋችን ዕለት ዘመዷን የተነጠቀች ሴት አገኘሁ። አንተ ነብሰ በላ ነህ አለችኝ'' በማለት ያጋጠመውን ነገር ሚርዋስ ያስታውሳል።
ሪሃናም ብትሆን በተለያዩ አጋጣሚዎች ሰዎች ጥፋተኛ እንደሆነች ነግረዋታል። ''አንቺና ባለቤትሽ በዛች በተረገመች ዕለት ሰርጋችሁን ባታካሂዱ ኖሮ ይሄ ሁሉ አይከሰትም ነበር'' የሚሏት በርካቶች ናቸው።
ምንም እንኳን አይኤስ ለጥቃቱ ኃላፊነቱን ቢወስድም በአፍጋኒስታን በኃይልም በተቀባይነትም ጥሩ ይዞታ ላይ የሚገኘው ታሊባን ነው። ታሊባንም ከአይኤስ ሲነጻጸር አነስተኛ ቁጥር ያለው ጥቃት ነው የሰነዘረው። እስካሁንም በአስርታት የሚቆጠሩ ጥቃቶችን በአፍጋኒስታን ፈጽሟል።
ባለፈው ግንቦት ወር ላይ ቡድኑ በዋና ከተማዋ ካቡል በአንድ ሆስፒታል ወላዶች ክፍል ውስጥ ፈጽሞታል በተባለው ጥቃት 24 ሴቶች፣ ህጻናትና አዲስ የተወለዱ ልጆች ተገድለዋል።
ሪሃና እና ሚርዋስ በተፈጠረው ነገር አሁንም ድረስ ስነ-ልቦናዊ ጫና ውስጥ የሚገኙ ሲሆን በነሱ ምክንያት እነዚያ ሁሉ ሰዎች መሞታቸው ደግሞ የጥፋተኝነት ስሜት ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል።
ነገር ግን ጥንዶቹ የደረሰባቸውን የአእምሮ መታወክ ለማስታገስ በማሰብ የስነ-ልቦና ባለሙያ ጋር እስከመሄድ ደርሰዋል። በአሁኑ ሰአትም ትልቅ መሻሻል እያሳዩ እንደሆነ እራሳቸው መስክረዋል።














