የሶማሊያ ልዩ ኃይል በሞቃዲሾ የሆቴል አጋቾቹን ደመሰስኩ አለ

copyrightREUTERS

ሞቃዲሹ

የፎቶው ባለመብት, REUTERS

አልሸባብ በትናንቱ ጥቃት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ገደለ።

አልሻባብ በሞቃዲሾ አንድ ሆቴል ውስጥ ትናንት ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ የአገሪቱ ልዩ ኃይል እገታውን አክሽፊያለው ብሏል፡፡

ትናንት እሑድ አልሸባብ ባደረገው ጥቃት በትንሹ 10 ሰዎች ተገድለዋል፡፡ ጥቃቱና እገታው የተደረገበት ሆቴል ኤሊት ሆቴል የሚሰኝ ሲሆን በሊዶ የባሕር ዳርቻ የሚገኝ ነው፡፡

ጥቃት አድራሾቹ መጀመርያ በሆቴሉ መግቢያ ላይ በተሸከርካሪ የተጠመደ ቦምብ ካፈነዱ በኋላ ወደ ሆቴሉ ዘልቀው በመግባት እንግዶቹን አግተዋል፡፡ ይህ በቅርብ ጊዜ ተመረቀ የተባለው ሆቴል የተገነባው በአንድ የሶማሊያ የምክር ቤት አባል በሆኑ ሰው ሲሆን ትልልቅ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ይዘወተራል ተብሏል።

የጸጥታ ኃይሎች አካባቢውን ካጠሩ በኋላ ከአጋቾቹ ጋር የተኩስ ልውውጥ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ከአራት ሰዓታት የተኩስ ልውውጥ በኋላ የመንግሥት ቃል አቀባይ የሆኑት ኢስማኤል ሙክታር ኡመር በትዊተር ሰሌዳቸው እገታው መክሸፉን ይፋ አድርገዋል፡፡ በዚህ የትዊተር መግለጫቸው ቃል አቀባዩ እንዳሉት አጋቾቹ ሁሉም 'ተደምስሰዋል'፡፡

እስካሁን ምን ያህል አጋቾች በዚህ ጥቃት እንደተሳተፉ የወጣ መረጃ የለም፡፡ ከሟቾቹ መካከል ከማስታወቂያ እና ከመከላከያ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሥልጣናት ይገኙበታል፡፡ ሌሎች በርካቶች በጥቃቱ ቆስለዋል፡፡

አንድ የግል የሶማሊያ የዜና አገልግሎት የሚሰጥ ድረገጽ እገታው የተካሄደበት ሆቴል በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ጥበቃና ፍተሻ የሚደረግበት እንደሆነ ጽፏል፡፡

የአልሸባብ እንደሆነ ከሚገልጽ አንድ የኢንተርኔት መልእክት ‹‹ሠራዊታችን አንድ ዘመቻ ላይ ነው። በምክር ቤት አባሉ የተገነባው ኤሊት ሆቴል ውስጥ የተሰዉ አባሎቻችን አሉ፡፡ ጥቃት እየዳረስንባቸው ያለነው ፈጣሪን የካዱትና የጥመት መንገድን የተከተሉት ላይ ነው›› ይላል፡፡

ከአልቃኢዳ ጋር በጥምረት የሚሰራው አልሸባብ በሶማሊያና አጎራባች አገራት ውስጥ ጥቃት ሲያደርስ ዐሥር ዓመት አስቆጥሯል፡፡

አልሸባብ በመንግሥት ኃይልና በአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል ትብብር ከፖለቲካው ገለል የተደረገ ቢሆንም አሁንም አልፎ አልፎ በአገሪቱ ላይ ጥቃቶችን የመሰንዘር አቅሙን አላጣም፡፡ በተለይም ባለፉት ሁለት ወራት የአልሸባብ ጥቃት በርትቷል፡፡

ባለፈው ሳምንት ለምሳሌ በአንድ ታሳሪ በነበረ የአልሸባብ አባልና በእስር ቤት ጠባቂዎች መካከል በነበረ መታኮስ 20 ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው አይዘነጋም፡፡ እስር ቤት ሳሉ የጦር መሣሪያ ማግኘት የቻሉ የአልሸባብ አባላት ከፍተኛ ጥበቃ ይደረግለታል ከሚባለው እስር ቤት ተታኩሰው ሊያመልጡ ሲሉ ነበር አደጋው የደረሰው።