ኮሮናቫይረስ ፡ በለንደን የኮቪድ-19 ስርጭት በመጨመሩ ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብ ሊጣል ነው

በአሁን ሰዓት በደረጃ ሁለት የእንቅስቃሴ ገደብ ውስጥ ያለችው ለንደን በሳምንቱ መጨረሻ ላይ አውራ ጎዳናዎቿ እና የመገበያያ ስፍራዎቿ በሰዎች ተሞልተው ታይተዋል

የፎቶው ባለመብት, PA Media

በእንግሊዝ ለንደን ከተማ የኮሮናቫይረስ ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ በመሆኑ ጥብቅ ነው የተባለ የእንቅስቃሴ ገደብ በመጪዎቹ ቀናት ሊጣል መሆኑን ቢቢሲ ከምንጮቹ መረዳት ችሏል።

የአገሪቱ ሚኒስትሮችና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በለንደን ከተማ ያለው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር "በእጅጉ እንዳሳሰባቸው" ሲገልፁ ነበር።

ቢቢሲ ከመረጃ ምንጮቹ መረዳት እንደቻለው የለንደን ከተማ የሕዝብ እንደራሴዎች ስለ ጉዳዩ የተነገራቸው ቢሆንም እስካሁን ድረስ ግን ምንም ዓይነት ውሳኔ ላይ አልተደረሰም ተብሏል።

የለንደን ከተማ ከንቲባ ሳዲቅ ካኻን ሚኒስትሮችን የከተማዋን ምጣኔ ሀብት በማይጎዳ መልኩ "በአስተውሎት" ውሳኔዎችን እንዲያሳልፉ ጥሪ አቅርበዋል።

እንደ ከንቲባው ከሆነ በከተማዋ ሦስተኛ ደረጃ የተባለው የእንቅስቃሴ ገደብ የሚጣል ከሆነ የአገልግሎት ሰጪ እና የቱሪዝም ዘርፉ ላይ ከፍተኛ የሆነ ተጽዕኖ ይኖረዋል።

አንዳንድ የከተማዋ ምክር ቤት አባላት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መጨመርን ተከትሎ "ከደረጃ ሦስት ከፍያለ" እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል።

ደረጃ ስት የእንቅስቃሴ ገደብ ምን ይዟል?

በለንደን ያለው የኮሮናቫይረስ ስርጭት መጨመሩን ተከትሎ ይጣላል የተባለው ደረጃ ሦስት የእንቅስቃሴ ገደብ በቤት ውስጥም ሆነ ከቤት ውጪ ከቤተሰብ አባላት በአንድነት መሆንን ይከለክላል።

እንዲሁም በመናፈሻ ስፍራዎች በባህር ዳርቻዎችና ከከተማ ውጪ እስከ ስድስት ሰዎች ድረስ በመሆን አብሮ ማሳለፍ ይቻላል።

የንግድ መደብሮች፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተሪያ ስፍራዎች እና የውበት ሳሎኖች ክፍት ሆነው ሊቆዩ ይችላሉ።

መጠጥ ቤቶች፣ ካፌዎች፣ ምግብ ቤቶች ግን ወደ ቤት ወስደው ለሚጠቀሙ ካልሆነ በስተቀር ዝግ ሆነው ይቆያሉ።

የስፖርታዊ ውድድር አፍቃሪዎች በስታዲየሞች ተገኝተው ውድድሩን መከታተል አይችሉም።

ሲኒማ ቤቶችም ሆኑ ሌሎች የቤት ውስጥ ስፖርቶች ዝግ እንዲሆኑ ይደረጋል።

የደረጃ ሦስት የእንቅስቃሴ ገደብ የተጣለበት ከተማ ነዋሪዎች ወደየትኛውም የአገሪቱ ክፍል እንዳይንቀሳቀሱ ይከለከላሉ።

የአገሪቱ የጤና ሚኒስትር ማት ሐንኮክ በዛሬው ዕለት ለእንደራሴዎች ምክር ቤት ንግግር የሚያደርጉ ሲሆን በማስከተልም መግለጫ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ በእንዲህ እያለ የለንደን ከተማ ከንቲባ መንግሥት በከተማዋ የሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና ኮሌጆች ከገና በዓል በፊት እንዲዘጉ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ሳዲቅ ካኻን እድሜያቸው ከ10 እስከ 19 የሆኑ ታዳጊዎች ላይ የኮቪድ-19 ስርጭት ከፍ ብሎ በመታየቱ ረዥም የእረፍት ጊዜ እንዲወሰዱ ይፈልጋሉ።

ባለፉት ሳምንታት በለንደን ከተማ ውስጥ እና ውጪ የሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች በከፍተኛ ቁጥር የኮሮናቫይረስ መጨመር ታይቶባቸዋል።

በኅዳር ወር ለንደን ዝቅተኛ የቫይረሱ ስርጭትን ካስመዘገቡ የእንግሊዝ ከተሞች መካከል አንዷ የነበረች ሲሆን አሁን ግን "ከፍተኛ" በተባለ ፍጥነት ቫይረሱ በከተማዋ እየተስፋፋ ነው።

የጤና ባለሙያዎች ለንደን የኮሮናቫይረስ ምክንያት የሚከሰት ሞትን ለመቀነስ በደረጃ ሦስተኛ የጥንቃቄ እርምጃ ላይ እንድትቀመጥ ሲወተውቱ ከርመዋል።

ምሥራቅ ለንደን እና የተወሰኑ የኢሴክስ ከተማ ክፍሎች የኮቪድ-19 ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ የታየባቸው ናቸው።