ኮሮናቫይረስ ፡ ትራምፕ የዋይት ሐውስ አባላት የኮቪድ-19 ክትባት ቀድመው ይወስዳሉ መባሉን ተቃወሙ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በቀጣዮቹ ቀናት ለዋይት ሐውስ ባለሥልጣናት የኮሮናቫይረስ ክትባት ለመስጠት የተያዘውን እቅድ መቀየራቸውን አስታወቁ።
ቀደም ብሎ ባለሥልጣናት የትራምፕ አስተዳደር ከፍተኛ ባለሙያዎች የፋይዘር/ባዮንቴክ ክትባት ከሚሰጣቸው ሰዎች መካካል እንደሚሆኑ ተናግረው ነበር።
ይሁን እንጂ ትራምፕ በእቅዶቹ ላይ ማስተካካያ እንዲደረግ መጠየቃቸውን ተናግረዋል።
አሜሪካ ክትባቱን ለድንገተኛ/ አስቸኳይ ጊዜ ለመጠቀም የፈቀደች ሲሆን ሥርጭቱ ዛሬ እንደሚጀምር ተገልጿል።
ይህ ክትባት ኮቪድ -19ን 95 በመቶ የመከላከል አቅም አለው ተብሏል።
የመጀመሪያው ሦስት ሚሊየን ክትባትም በመላው አሜሪካ በ50 ግዛቶች በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ተሰራጭቷል።
የመጀመሪያው ክትባት ጭነት እሁድ እለት ሚሽጋን ከሚገኝ ተቋም ተንቀሳቅሷል። የመጀመሪያውን ክትባትም አረጋውያንና ጤና ባለሙያዎች ያገኛሉ ተብሏል።
እሁድ ዕለት የዋይት ሐውስ አባላት ክትባቱን በቅድሚያ ከሚያገኙ ሰዎች መካካል ይገኙበታል መባሉ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ትችትን አስከትሏል።
ትራምፕም የተያዘውን እቅድ ለምን ለመቀየር እንደወሰኑ እንዲሁም መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ከወረርሽኙ ለመጠበቅ በሚያደርገው ጥረት ላይ ምን ዓይነት ተፅዕኖ እንደሚኖረው ግልፅ የሆነ ነገር የለም።
በአሜሪካ ካለፈው ኅዳር ወር ጀምሮ የኮሮናቫይረስ ሥርጭት እየጨመረ ነው። በአገሪቷ ቅዳሜ ዕለት በዓለም ከፍተኛ የተባለው ዕለታዊ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 3 ሺህ 309 ሆኖ ተመዝግቧል።
ታዲያ የክትባቱ መሰራጨት መጀመሩ ወደ 30 ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈውን ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል ወሳኝ ምዕራፍ ሆኗል።
የአገሪቷ የምግብና መድኃኒት አስተዳደር (ኤፍዲኤ) ከትራምፕ አስተዳደር ከፍተኛ ጫና ከተደረገበት በኋላ ክትባቱን ለአስቸኳይ ጊዜ መጠቀም እንደሚቻል ፈቃድ የሰጠው አርብ ዕለት ነበር።
ይህ ክትባት በዩናይትድ ኪንግደም ቀደም ብሎ እየተሰጠ ነው። የፋይዘር ክትባትም በካናዳ፣ በባህሬን እና በሳዑዲ አረቢያ ፈቃድ አግኝቷል።
ትራምፕ መቼ ይከተባሉ?
ባለሥልጣናት ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እንደገለፁት የተወሰኑት የመጀመሪያዎቹ ክትባቶች ከትራምፕ ጋር በቅርበት ለሚሰሩ ሰዎች እንደሚቀመጥ ተናግረው ነበር።
ይህንኑ ክትባቱን በቅድሚያ ለዋይት ሐውስ አባላት ለመስጠት የታሰበውን እቅድ መጀመሪያ የዘገበው ኒው ዮርክ ታይምስ ሲሆን የብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ ጆን ኡልየት ይህንኑ አረጋግጠዋል።
የፕሮግራሙ ዋነኛው ዓላማም ማኅበረሰቡ በክትባቱ ላይ እምነት ማጎልበት ነበር ብለዋል።
"የአሜሪካ ሕዝብ በማኅበረሰብ ጤና ባለሙያዎች እና በብሔራዊ ደኅንነት አመራሮች ምክር መሰረት ከአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር አንድ ዓይነት፣ ደኅንነቱ የተጠበቀና ውጤታማ የሆነ ክትባት እንደሚሰጥ እምነት ሊኖረው ይገባል" ብለዋል ቃል አቀባዩ።
ይሁን እንጂ ፕሬዚደንት ትራምፕ እሁድ እለት ባለሥልጣናት ክትባቱን ለመውሰድ ረዘም ያለ ጊዜ መጠበቅ እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ፕሬዚደንቱ "በዋይት ሐውስ የሚሰሩ ሰዎች አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር፤ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ነው ክትባቱን መውሰድ ያለባቸው" ሲሉ በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል። ይህ እቅድ እንዲስተካከልም ጠይቄያለሁ ብለዋል።
ጥቅምት ወር ላይ በኮሮናቫይረስ ተይዘው ሆስፒታል ከገቡ በኋላ ያገገሙት ፕሬዚደንቱ፤ ክትባቱን ለመውሰድ ገና እንዳላቀዱ ገልፀው፤ በተገቢው ጊዜ ይህንን ለማድረግ በጉጉት እንደሚጠባበቁ ተናግረዋል።
ቀደም ብሎ ፕሬዚደንቱ በሽታ የመከላከል አቅም አዳብሬያለሁ ብለው ነበር።
የሕክምና ባለሙያዎች ግን ከኮቪድ-19 ያገገሙ ሰዎች ዳግም ሊያዙ መቻል አለመቻላቸው ግልፅ አይደለም፤ ቢሆን እንኳን እስከመቼ የሚለው እንደማይታወቅ አስታውቀዋል።
በዋይት ሐውስ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተከስቶ ነበር። በርካታ ከፍተኛ ሠራተኞችም የቫይረሱ ተጠቂ ናቸው። ለመጨረሻ ጊዜ በቫይረሱ የተያዙት የትራምፕ የግል ጠበቃ ሩዲይ ጁሊያኒ ሲሆኑ ባሳለፍነው ሳምንት ትራምፕ በወሰዱት ተመሳሳይ መድኃኒት ሕክምና እየተደረገላቸው እንደሆነ ገልፀው ነበር።
















