ኮሮናቫይረስ፡ የዋይት ሃውስ አባላት ክትባቱን ቀድመው ሊወስዱ ነው

ትራምፕ እና ማይክ ፔንስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በትራምፕ አስተዳደር ውስጥ ከፍተኛ ባለስልጣናት የሆኑ የዋይት ሃውስ አባላት ክትባቱን ቀድመው ከሚወሰዱት አሜሪካውን መካከል እንደሚሆኑ ተገለጸ።

አሜሪካ የፋይዘር/ባዮንቴክ ሰራሹን የኮቪድ-19 ክትባቶቹን "ወደ ሁሉም ግዛቶቿ" ማከፋፈለች መጀመሯ ተገልጿል።

አሜሪካ ዜጎቿን ዛሬ መከተብ የምትጀምር ሲሆን እስከ መጋቢት ማገባደጃ ድርስ 100 ሚሊዮን ሰዎችን ለመከተብ ታቅዷል ተብሏል።

የአሜሪካ ባለስልጣናት ክትባቱን ቅድሚያ የሚያገኙት ለበሽታው የበለጠ ተጋላጭ የሆኑት የጤና ባለሙያዎችና በእንክክብካቤ ማዕከላት የሚገኙ አረጋውያን ናቸው ብለው የነበረ ቢሆንም አሜሪካ መገናኛ ብዙሃን የዋይት ሃውስ ባለስልጣናትን ጠቀሰው እንደዘገቡት የዋይት ሃውስ አባላት ክትባቱን ቀድመው ከሚወስዱ አሜሪካውያን ተርታ ተሰልፈዋል።

አንድ ስማቸው ያልተጠቀሰ የአሜሪካ ባለስልጣን ለሮይተርስ እንደተናገሩት፤ የዋይት ሃውስ አባላት ክትባቱን ቀድመው ማግኘታቸው የመንግሥት ሠራዎች ሳይቋረጡ እንዲከናወኑ ይረዳል።

በመጀመሪያው ዙር ክትባቱን የማከፋፈል ሥራ ለ3 ሚሊዮን ዜጎቿ የሚሆን ክትባቶች በመላው የአሜሪካ ግዛቶች እየደረሰ ነው። የክትባት ስርጭቱን በበላይነት የሚቆጣጠሩት የአሜሪካ ጦር ጀነራል ጉስታፍ ፔርና ዛሬ ሰኞ ክትባቱ በአሜሪካ 145 ቦታዎች ይላካል ብለዋል።

ክትባቱ በግዙፍ አውሮፕላኖች እየተከፋፈለ ይገኛል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ክትባቱ በግዙፍ አውሮፕላኖች እየተከፋፈለ ይገኛል

ነገ እና ከነገ በስቲያ ደግሞ ክትባቱ ወደ ተጨማሪ 491 ቦታዎች ይላከል ብለዋል ጀነራል ጉስታፍ። አሜሪካ ፋይዘር/ባዮንቴክ ያበለጸጉትን የኮሮናቫይረስ ክትባት ለአስቸኳይ ጊዜ አገልግሎት እንዲውል ፍቃድ መስጠቷ ይታወሳል።

ይህ ክትባት የኮሮናቫይረስ በሽታን በመከላከል 95 በመቶ አስተማማኝ መሆኑ ተገልጿል። ይኸው ተመሳሳይ ክትባት በዩኬ ጥቅም ላይ መዋል የተጀመረ ሲሆን በካናዳ፣ ባህሬንና ሳዑዲ አረቢያም ፈቃድ አግኝቷል።

በኮሮናቫይረስ ክፉኛ እየተጠቃችው ባለው አሜሪካ ከትናንት በስቲያ ብቻ 3 ሺህ 309 ዜጎቿን አጥታለች።

አኃዙን ሪፖርት ያደረገው የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ ድረገፅ የበለጠ እንደሚያስረዳው በአለም ላይ ከፍተኛ በቀን የተመዘገበ ሞትም አድርጎታል።

የፋይዘር/ባዮንቴክ የኮሮናቫይረስ ክትባትን ለአስቸኳይ ጊዜ መጠቀም ፍቃድ እንዲያገኝ በከፍተኛ ሁኔታ በትራምፕ አስተዳደር ጫና የተደረገበት የምግብና መድኃኒት አስተዳደርም ውሳኔውን የወረርሽኙ "አዲስ ምዕራፍ" ብለውታል።