የጆ ባይደን ባለቤት "ዶ/ር" ተብለው መጠራታቸው እያጨቃጨቀ ነው

የተመራጩ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ባለቤት ጂል ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የተመራጩ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ባለቤት ጂል ባይደን

የተመራጩ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ባለቤት እና አዲሲቱ ቀዳማዊ እመቤት ለስማቸው ቅጽል "ዶክተር" የሚለውን መጠቀም አለባቸው ወይ የሚለው በአሜሪካ ማህበራዊ የትስስር መድረክ አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኗል።

ጉዳዩ ማነጋገር የጀመረው ጆሴፍ ኤፒስቴን የተባለ አምደኛ በዎልስትሪት ጆርናል ጋዜጣ አንድ ጽሑፍ ማሳተሙን ተከትሎ ነው።

ይህ አምደኛ በጋዜጣው ባሰፈረው ሐሳብ ጂል ባይደን ራሳቸውን "ዶክተር ጂል ባይደን" እያሉ መጥራታቸው አሳፋሪ ነው፤ ትክክልም አይደለም፤ እናም 'ክብርት ቀዳማዊት እመቤት እባክዎ ራሱን አደብ ያስገዙ' የሚል ይዘት ያለው ጽሑፍ ጽፏል።

ይህ ሐሳብ ያስቆጣቸውና አሉታዊ ጾተኝነት ነው ያሉ ጉዳዩን ወደ ማኅበራዊ የትስስር መድረክ ወስደውታል።

አምደኛው የመጪዋን ቀዳማዊት እመቤት በትምህርት ያገኙትን ዶክትሬት ከክብር ዶክትሬት ጋር በማመሳሰል ጽፏል።

"ዶ/ር ጂል ባይደን ቀልደኛ ናቸው። ራሳቸውን በግድ ዶክተር ብለው የሚጠሩ ኮሚክ ሴትዮ" ሲል ተሳልቆባቸዋል ይህ ጎምቱ የአካዳሚክ ሰው በዎልስትሪት በጻፈው ሐሳብ።

ይህ የአምደኛው ሐሳብ ያበሳጫቸው ሰዎች አምደኛውን በአሉታ ጾተኝነት ከሰውታል። ይህ ለሴቶች ያለውን ንቀት ብቻ የሚያሳይ ነው፤ አሳፋሪም ነው ብለዋል ብዙዎች።

ጂል ባይደን ዶክተር የሚለውን የአካዳሚክ ቅጽል በትዊተር ገጻቸው በይፋ ይጠቀሙታል። ይህ ዶ/ር ወይም ፕሮፌሰር መባባሉ ከዩኒቨርስቲዎች አውድ ውጭ እምብዛምም የተለመደ አይደለም።

ጂል ዶክትሬታቸውን ያገኙትም ከደላዌር ዩኒቨርስቲ እአአ 2007 ላይ ነበር። የመመረቂያ ጽሑፋቸውን የጻፉትም በማኅበረሰብ ኮሌጆች ውስጥ ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ተማሪዎችን እንዴት መታደግ ይቻላል በሚል ርእስ ነበር።

ከዚህም በላይ ጂል ባይደን ሁለት የማስተርስ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን በአሜሪካ ታሪክ ብዙ ርቀት በትምህርት ከገፉ ቀዳማዊት እመቤቶች ተርታ በቅርቡ ይመደባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ያም ሆኖ በዎልስትሪት ጆርናል ሐሳቡን ያሰፈረው አምደኛው ጂል ባይደን ላይ ተዘባብቶባቸዋል።

"አንድ ብልህ ሰው ምን አለ መሰለሽ? አንድ ሰው አንድ ልጅ እንኳ ሳያዋልድ ራሱን ዶክተር ብሎ ባይጠራ እመክረዋለሁ!"

አምደኛው ኤፕስቴይን የ83 ዓመት ሰው ሲሆን በአካዳሚክ ዘርፍ ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ሰዎች የሚመደብ ነው።

"እባክዎ ዶ/ር ጂል ራስዎን ዶ/ር እያሉ ማቄል ያቁሙ" ብሏቸዋል መጪዋን ቀዳማዊት እመቤት።

የአምደኛውን ሐሳብ ካጣጣሉት ሰዎች መካከል የጥቁሮች መብት ተሟጋች የነበረው የማርቲን ሉተር ኪንግ ጁንየር ትንሽ ልጅ በርኒስ ኪንግ ትገኝበታለች።

"አባቴ ዶክተር ኪንግ ተብሎ ይጠራ የነበረው ሐኪም ስለነበረ አይደለም፤ ነገር ግን ተግባሮቹ ብዙዎችን ፈውሰዋል" ስትል በትዊተር ሰሌዳዋ ላይ ጽፋለች።

ተመራጭዋ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሐሪስ በበኩሏ "ዶ/ር ጂል ዶክትሬቷን ያገኘቸው ገዝታ ሳይሆን በጥረት ነው። ለኔም ለተማሪዎቿም ሆነ ለአሜሪካዊያን ትልቅ አርአያ ናት" ብላለች።

ብዙዎች የአምደኛውን ሐሳብ "ዶ/ር ጂል ሴት በመሆናቸው የተሰነዘረ ንቀት እንጂ ሌላ አይደለም ሲሉ" ከአሉታ ጾተኝነት ጋር አስተሳስረውታል።

ሐኪም ሳይሆኑ በሌላ ዘርፍ ራስን "ዶ/ር" ብሎ መጥራት በአሜሪካ እምብዛምም የተለመደ ባይሆንም ከዚህ ቀደም በኒክሰን ጊዜ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ሄንሪ ኪሲንገር ባልታወቀ ምክንያት ራሳቸውን ዶ/ር ኪሲንገር ብለው ይጠሩ ነበር። ብዙ ሚዲያዎችም ይህንኑ አጠራር ይከተሉ ነበር።

"ዶክተር" የሚለው ቃል ከስም ቅጥያ ጋር አብሮ አገልግሎት የሚውልበት አግባብ በብዙ አገራት በሕክምና ለተመረቀ ሰው ብቻ ነው የሚውለው።

ሆኖም በትምህርት ተቋማት የሚሰሩ መምህራንና ተመራማሪዎች ሦስተኛ ዲግሪ ከሰሩ በኋላ በትምህርታዊ አውድ ብቻ ይህንኑ ቅጽል ይጠቀማሉ። ሆኖም በይፋ በሌላ አውድ ላይ ዶክተር ሲሉ ራሳቸውን አይጠሩም።

የጂል ባይደን ጉዳያ አነጋጋሪ የሆነውም ከሕክምና ውጭ ባሉ ዘርፎች በሦስተኛ ዲግሪ ስለተመረቁ ብቻ ራሳቸውን ዶክተር ብለው በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ መሰየማቸው ነው።

ቢቢሲ የውስጥ የስም አጠራር ደንብ እንደሚለው አንድ ግለሰብ "ዶ/ር" የሚል መጠርያ በዜናዎች ላይ ከስሙ ጋር አብሮ ለመጠቀም በሕክምና ወይም ደግሞ በአንዳንድ ቤተክርስቲያን አገልግሎት ዘርፍ የዶክትሬት ዲግሪ የያዘ መሆን ይኖርበታል ይላል።